
By Admin
እንደ ንጉስ እልፍኝ … በከተማ ላይ ከልካይ ሹም ሾሞ ደስ ባለው ቀን ተነስቶ “ኣማራ ከሆንክ ተመለስ” እያለው፣ ወገኑን “መጤ ነህ – ሰፋሪ” እያስባለ እንደ ወገራ እንጨት በገጀራ እያስፈለጠለት … ዛሬ ክልሌ መጣ ብሎ የፈረስ ጭራ ወጥሮ ጮቤ ይረግጣል። እንደ ኣማራ ያለ ማን አለ?!
ትላንት፦ ሶሻል ሚዲያው ላይ ለዚህ ፅሑፍ feature image ያደረኩትን ፎቶ ስመለከት ከደቂቃ በላይ አጥፍቻለሁ። እነዚያን የብሽቀትና የመገረም ስሜት የተሞሉ በርካታ ሰከንዶች ግን እንዲሁ እንዳልባሌ ላልፋቸው አልፈለኩም። ስለዚህም ከጊዜ ላይ ጊዜ ተበድሬ፥ ይህን ኣጭር ፅሑፍና ግጥም ጽፌ ላጠፋሁት ጊዜ ዕዳዬን ከፈልኩ።
ከዓመታት በፊት በ Oprah Winfrey Talk Show ላይ በተመለከትኩዋት ኣንዲት የአይሁዳዊ ሴት ታሪክ ልጀምር። የዕድሜዋን ልክ በትክክል ባላስታውሰም፥ እስከ አሁን ድረስ ከኣይኔ ላይ ባልጠፋው ተክለ ቁመናዋ ግን ከወጣትነት የዕድሜ ክልል አልፋ በጎልማሳነት ወሰን ውስጥ ነበረች። በፕሮግራሙ ላይ ለመቅረቡዋም ዋናው ምክንያት፦ ምንም እንኳ ዕድሜዋ ገፋ ቢልም ትዳር መስርታ የራሱዋን ህይወት ለመምራት እምቢተኛ በመሆኗ ነው።
በሰሜን አሜሪካ እጅግ በጣም ሀብታም ከተባሉ ቤተሰቦቿ ጋር የምትኖረው ይህች ሴት፦ ለትዳር ጓደኝነት የምትመርጠው ወንድ መመዘኛ ከመደበኛው መስፈርት ወጣ ያለ ስለነበረ … “ትመከር” ብለው ነው ወላጆቿ ወደ Oprah Winfrey የላኩዋት። አጅሪት ግን በአእምሮዋ ስላ፣ በልቧ ቀርፃ ካሰቀመጥችው መመዘኛ አንዲትም ስንዝር ፈቀቅ አላለችም፤ እኔ ማግባት የምፈልገው ወንድ “አይሁዳዊ፣ ቢያንስ ከቤተሰቦቼ የገንዘብና የንብረት ይዞታ ጋር የሚመጣጠን ሀብት ያለው ብቻም ሳይሆን በሞያው የሆሊውድ ፊልም ዳይሬክተር መሆን ይኖርበታል” ባይ ነች። ታዲያ፦ Oprah Winfrey “እንዴት ነው ፍቅር … ዘርና ሙያ ይጠይቃል እንዴ?” ብላ ሞገተች። ሞልቃቃዋ ዶለዝ አይሁዳዊትም “አዎን፥ የእኔ ምርጫ እንደዚህ ነው” ስትል መለሰች። አንጋፋዋ የቶክሾው ንግስት Oprah Winfrey በመገረም እየተመለከተቻት “እሺ ሀብታምና ዝነኛ የሆነ አይሁዳዊ ማግኘት ይቻል ይሆናል፥ ነገር ግን አይሁዳዊ የሆነ የሆሊውድ ፊልም ዳይሬክተር ማግኘት ከባድ አይሆንም?” ስትል ሁለተኛ ጥያቄዋን አስከተለች። ይሄኔ … ከሆሊውድ ውጭ የሚመጣ ባል ወድ ውጭ … ባይዋ ሴት ፈርጠም ብላ “ቢከብድም … የእኛ የአይሁዶች ባህልና አመለካከት ከጥቁር አሜሪካውያን ማህበረሰብ የተለየ ነው” አለች።
ነገሩን በኣጭሩ ለማስቀመጥ፦ ግለሰቡዋ “የእኛ ባህል ከጥቁር አሜሪካውያን ባህልና አስተሳሰብ በጣም ይለያል” ያለችበትን ምክንያት ስታሰረዳ፦ “ጥቁር አሜሪካውያን በትምህርት፣ በሀብትና ዝና ከፍ እያሉ በሄዱ ቁጥር ለትዳር አጋርነት የሚመርጡት ሚስት ወይንም ባል የነጭ ዝርያን (white race) ነው። የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ማለት ወይንም መሻሻል የሚለኩበትና የሚያሳዩበት መንገድ ከማህበረሰባቸው ውጭ ነጭ ሴትን ወይንም ወንድን “date” በማድረግና በማግባት ሲሆን፤ እኛ አይሁዳውያን ግን ከዚህ በተለየ መልኩ በትምህርት፣ በሀብትም ሆነ ዝና ከፍታን እየጨመርን በሄድን ቁጥር አብሮ መኖር የምንፈልገው (የምንመርጠው) ከራሳችን ማህበረሰብ – ከአይሁዳዊ ወገን ነው። ለዛም ነው በኑሮ ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ ከሆኑት ጥቂት አይሁዳዋያን በስተቀር በከፍታ ላይ ባለው አይሁዳዊ ማህበረሰብ ውስጥ interracial marriage (ቅይጥ የዘር ጋብቻ) የማይታየው” ብላ፥ የ O.J. Simpson, የ Tiger Woods, እና የሌሎች ዝነኛ ጥቁር አሜሪካውያንን የትዳር ህይወት እንደምሳሌ በመጥቀስ ተከራክራለች።
እኔም ታዲያ … አሁን ላይ … ከየክፍለሀገሩ በፖለቲካ ሹመትና አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡትን የኣማራ ፖለቲከኞች ስመለከት የዛችን አይሁዳዊት ሴት “ጥቁር አሜሪካውያን” መስለው ታዩኝ። ትንሽ ከፍ ሲሉ ማህበረሰባቸውን የሚረሱ፣ መሐል ሀገር መኖርን እንደ ትልቅ ክብር የሚቆጥሩ፣ ለስልጣንና ለማይሞላ ሆዳቸው የዘጠኝ ወር መኖሪያቸው የነበረውን የእናታቸውን ሆድ የሚረግጡ፣ ከተሜነት ሥር መሠረታቸውን የሚያስነቅላቸው (የሚያስረሳቸው)። ከወትሮው በተለየ እጅግ በሚዘገንን ጭካኔ ዘር ማንዘራቸው እየተቆጠረ እንደ ኣውሬ ሲታደንና ሲታረድ፥ እነርሱም ከወትሮው በበለጠ መጮህና መናገር ሲገባቸው … ጭራሽ … “ዝም ለማለት ቃል ኪዳን አስሬያለሁ” የሚሉ ከንቱዎች።
ይህ ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የጠቅላይ ሚንስትሩም ትዝብት ስለሆነ ነው … በኣንድ የምክር ቤት መድረክ ላይ አቶ ክርስቲያን ታደለን “ውክልና የሰጦት ህዝብ ጠፍተውበት እያፈላለጐት ነው” የሚል ዘይቤ ባለው አግቦ ያስገቡላቸው። በነገራችን ላይ፦ በብኣዴን እና በኣብን መካከል የ “ዴ” ፊደል እንጂ ምንም ዓይነት የትርጉም ለውጥ የለም፤ ያኛው ሎሌ ይኼኛውም ጀሌ ነው። እናም … ከዚህ በታች ያለችው ግጥም መታሰቢያነቷ ለሁለቱም ትሁንልኝ።
ስምስ ኣማራ ያውጣ
ስምስ ኣማራ ያውጣ
ለባሽ ያሉት ፎጣ!
አይሳሳም ለቃላት
አይፈራም ፊደላት!
ምግባር መቼ ከብዶት
ተግባር መቼ ገዶት?
ፈሪን አጀግኖ … የሌለውን ክቦ
ኮሳሳ፣ ቀጭኑን … አግዝፎ፣ አደልቦ
መዠርጥጥጥጥጥ ያደርገዋል … ከስምም ስም ስቦ!
አሽከሩን – “ንጉሱ” … ጎዶሎውን – “ሞላ”
ሲለው መች ያፍርና?
ለኣንድ ራሱ ያልቆመን
ጠውላጋ አረም፣ ጎመን
ግንድ፣ ሥር አብቅሎ … ያለብሰዋል “ግርማ”
ሊለው “የሺጥላ”
ስም ቀጭቶ እንደ አክርማ!
ስምስ ኣማራ ያውጣ
ለባሽ ያሉት ፎጣ!
ፈጣሪንስ ቢሆን … መች ያማርረዋል?
ሲነሳው ዘር፣ ፍሬ … “አገኘሁ” ብሎ ያድራል!
ሲሰጠውም መርገምት
ቆጥሮ እንደ “በረከት”
“ተመስገን” ይለዋል … “ጥሩ” እንዳረገለት!
ጌኛዋን ሸላልሞ … መፍዙዙን አድምቆ
“ሞገስ”፣ ድሪ ጭኖ … “መኮንን” አስንቆ
“ዳግማዊት” “ደመቀ” … “ይልቃል” ሲል ጠርቶ
በድን ያራምዳል … ከስምም ስም ሰጥቶ
ደሞ ስም ለማውጣት…
ኣማራን ማን ብሎት?!