Post

የኣዲስ አመት ምግባር

የኣዲስ አመት ምግባር

By Admin

ዓመትን ዓመት የሚያሰኘው የቀናት ድምር ነው። በዚህ ከተስማማን ደግሞ እያንዳንዷ ቀን ትናንሽ ዓመት ናት ብል አያከራክረንም። የሰው ልጅ በህይወቱ የመልካም ጅማሬ መሠረት ለመጣል ግዴታ ቀናት ተራብትው አዲስ ዓመት መወለድ የለበትም። “እና?” ካላችሁኝ ደግሞ … ለእኔ የአዲስ አመት ዕቅድ (New Year Resolution) ትርጉም የለሽ ነው።

ለሚያስብ አዕምሮ፥ ክፉውን አቁሞ መልካሙን ለመጀመር ግዴታ ወራት ዞረው ዓመት መምጣት የለበትም። ለጐጂ ልማድም ሆነ አመለካከት መደምደሚያ አበጅቶ ጠቃሚውን “ኣሀዱ” ብለን መትጋት ያለብን በየዓመቱ ዋዜማ ሳይሆን በየቀናቱ ማለዳ፣ ዘወትር መሽቶ ሲነጋ ሊሆን ይገባዋል ባይ ነኝ።

ያም ቢሆን ግን … እስቲ 2017 ጨዋ እና ቅን ድርጅታዊ የትግል ስነ ምግባር ለመጀመርከግለኝነትና ከስልጣን ፍትወት የፅዳ ፖለቲካ ለማራመድ ኣዲስ ኪዳን የምናስርበት ዓመት ይሁን ለማለት ወደድኩ።

በእርግጥ መንገዶች ሁሉ ወደ … ያመራሉ  እንደሚባለው የትግል መስመሮች ሁሉ ወደ ነፃነት (ትልማዊው ግብ) ያደርሳሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ትግል ወጣ ውረድ ብቻ ሳይሆን በግራም በቀኝ እልም ጭልጥ አድርጎ ያልታሰበ ደሴት ላይ የሚያራግፍ ብዙ ውስብስብ ሰርጥ እና ሸፍጥ የተሞላ ነው። ሀገራችን አሁን ያለችበትን ተጨባጭ እውነታ ስንመለከት ግን፡ የትኛውምንም የትግል ታንኳ የምንቀዝፍ መንግደኞች፡ መድረሻ ወደባችን ላይ ተማምነን በመከባበር መጓዝ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ይሆናል። ለአርነትም ይሁን ለማንነት የሚደረገውን ትንንቅ ለማገዝ ቆመናል የምንል ዜጎች፥ በማይራራቅ የትግል ግብ እና ስልት እርስ በእርስ ስንታኮስ፥ እነ ሰምሃል መለስ ከአልጋ ወደ ወንበር-ወራሽነት፣ ከዘውድ ወደ ዘንግ አገዛዝ አሸጋግረው ሲቀጠቅጡን ሊኖሩ በድብቅ እንደተማማሉ በአደባባይ ሲተማሙ ሰምተናል።  

ለእኔ እንደሚገባኝ፦ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ማህበራዊ ትዳር (ስብስብ) ውስጥ በአመራርም ሆነ በአባልነት ደረጃ ለመካተት፥ ከራስ ጋር መፋታት ቀዳሚና መሠረታዊ መስፈርት ነው፤ ከእኔነት በፊት እኛነት፣ ከግል አምሮት ይልቅ የወል ፍላጐት መቅደም ስላለበት። በሌላ አነጋገር፦ የአንድ ድርጅት ደጋፊ ወይንም መሪ ለመሆን የድርጅቱን አቋም (political orientation) ከመመርመር በፊት የራስን ስነ ልቦናዊ ዝግጅት በመፈተሽ፥ ግላዊ ፍላጐትን ለቡድን ጥቅም መስዋዕት ለማድረግ መዘጋጀትን ማረጋገጥ ይቀድማል። በየጊዜው ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ድርጅትን ለለውጥ ሳይሆን ለስልጣን መሳሪያነት የሚፈለፍሉ ወይንም የሚቀላቀሉ ግለሰቦች ይህንን ሀቅ አምነው ሊቀበሉት ይገባል።

ትላንት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ሆነን፥ ስልጣን በጥቂት ግለሰቦች ተጠቅልሎ ከሀገራችን የብሔራዊ መዝሙር ስንኝ ይልቅ የመሪዎቻችን ሀላፊነት እንደ አንቀፅ ረዝሞ በቃል ለመሸምደድ ይከብደን ነበር። ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ የኢፌዴሪ …ብለን ገና ስንጀምር ፊደል ያጥረን ነበር። ዛሬ ደግሞ አንዲቷን የስልጣን ወንበር ለአራት እና ለኣምስት መወረር ሙድ (mood) ሆኗል። ምክንያቱ ምንድን ነው ብለን እንቀበል? የችሎታ ማነስ ወይንስ የስልጣን ሱስ? አለመተማመን ከሆነስ ቀድሞውኑ አብሮነቱ ለምን አስፈለገ?

ለስልጣን ያለንን ለከት የለሽ ፍላጐት ከመግረዝ በተጨማሪ፥ በዚህ ኣዲስ ዓመት ኣዲስ የፖለቲካ ባህሪ ልናሳይበት ይገባል ብዬ የማምነው የማይገነባ ትችት እና አላስፈላጊ ዘለፋ በመወራወሩ ላይ ነው። ሀላፊነትና ተቆርቋሪነት የሚሰማን ዜጐች በትግል መደብ ልዩነት የተነሳ እንደ ዝሆን ሁለት ጥርስ እስኪቀረን ድረስ እርስ-በእርስ መነካከሱን መተው ይበጀናል። ልብ በሉ! አፍራሹን እንጂ ገንቢውን ሂስ እና ተቃውሞ አይደለም እናቁም እያልኩ ያለሁት።

ለምሳሌ እኔ፥ ዛሬም እንደ ትላንቱ በሥነ-ፍጥረትም ሆነ በፖለቲካ ትግል እምነቴ ኢቮሉሽኒስት (evolutionist) አይደለሁም። በራሱ ተፈጥሮአዊ ሂደት ታንክ ትራክተር፣ ጥይት ደግሞ ማንኪያ ይሆናል የሚል ከንቱ ቅዥት የለኝም። ክሬሽኒስት (creationist) ነኝ! ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ታጋዮች በትግል ይፈጥሩታል እንጂ በአዝጋሚ የፖለቲካ ኡደት አምባ-ገነን አገዛዝ በራሱ ወደ ሀገር-ገነን ሥርዓት ይቀየራል የሚል ፍልስፍና የለኝም። ሺህ አመት ብንጠብቅም የዚህ ለውጥ (evolution) ምስክሮች ልንሆን አንችልም። በተለይም እንደ ህወሃት ያለ ዘር-ገነን አገዛዝ፥ በብሔራዊ ምርጫ ይወገዳል ብዬ በማሰብ ከሰላማዊ ትግል ደጋፊዎች ረድፍ ከምቆምበበለጬ በርጫ እንጥለዋለን ብለው ከሚያፌዙት የወሎ ሰፈር ወጣቶች ጋር “ቄማ” ብቀመጥ እመርጣለሁ። ይህ አመለካከትና አቋሜ ግን የሰላማዊ ትግል ደጋፊዎችን አፍራሽ በሆነ መልኩ ለመንቀፍም ሆነ ለማደናቅፍ ምክንያት ሊሆነኝ በፍጹም አይችልም። እንደ ኣንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ግን፦ ህወሃት በጦር የሚቆስል እንጂ በምክርና ዝክር የሚሰበር ልብ የለውምና ንቁ! አውቆ-የተኛ አትሁኑ! ብሎ ማሳሰብ መብትም ግዴታዬም ይሆናል።

በተመሳሳይም፥ በሰሜን በኩል መሳሪያ አንስተናል ያሉትን ሀይሎች የምደግፍበት ምክንያት ምርጫቸው መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያገናዘበ ስለሆነ ብቻ እንጂ እስከዚች ደቂቃ ድረስ ሲፋለሙ ተመልክቼ – ተመስጬ አይደለም። ሜዳው ውስጥ ገብተን “ፊሽካው ተነፍቷል” ያሉን ተጫዋቾች በጠቅላላ በረኞች ሲሆኑ፥ ምነው የጐንደርና የጐጃም አልፎም የኢትዮጵያ ህዝብ ሲያልቅና በድረሱልን ጥሪ ሲማፀናችሁ፥ ዙሪያችሁን በነጭ ኖራ (ፔናሊቲ መስመር) አጥራችሁ ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ ከክልሉ የማይወጣ ጎል-ጠባቂ ብቻ መሆናችሁ? ብሎ መጠየቅ ወቅታዊም አግባብም ነው። ህወሃትን የመሰለ የቢልዮን ብር ጠላት ስልጣን ላይ ጐልቶ ግን፥ ተልካሻ ለሆነ ግላዊ ፖለቲካ – ህዝብንና ህዝባዊ ዓላማን ዋሻ በማድረግ ለስድብና ለስም ማጥፋት ዘመቻ ቤተ-አማራውን “ክተት!” ብሎ ነጋሪት መጎሰም የትም አያደርስም። እናስተውል! የጐንደር ህዝብ “የኦሮሞው ደም የእኔም ደም ነው” ሲል ያነሳው መፈክር፥ ዘረኛው ህወሃት የተቆጣጠረው የኣማራውን መሬት እንጂ የኣማራውን አእምሮ እንዳይደለ፣ ዛሬም ከ 25 ዓመት ቦኃላ ስነ-ልቦናው እና ምግባሩ በዘር መርዝ እንዳልተመረዘ አመላካች ነው።

ከዚህ ባሻገር ግን፥ ጥቁር ዩኒፎርም ለብሶ ባናየውም፥ ጊዜ ሁሌም ቢሆን ከከጨዋታ ሜዳ የማይጠፋ፣ አድሎ የማያውቅ ዳኛ ነውና ያለንን ግለሰባዊ በደልና ቁርሾ በይደር ማስቀመጡ አይከፋም። ከድል ቦኃላ፥ ቀናቶች ቀና ሲሆኑ ከግንቦት ሰባት ጋርም ሆነ ከሰባዎቹ ጋር በተንተረከከ ፍም የነሐሴን በቆሎ እሸት እየጠበስን የምንጨዋወተው ብዙ-ብዙ የእሳት ዳር ወጐች ይኖሩናል። እስከዛው ግን በዚህ የአሮጌው-ዓመት-መታሰቢያ ግጥም የዛሬ ጽሑፌን ላጠቃልል

እንደ ሽል አይገፋ
እንደ ቂጣ አይጠፋ
ያረገዝነው ተስፋ
ዛሬም እንደ-አበጠ  
     ቀን እየቀለጠ
ኣንድ ዓመት ነጐደ … ሄደ ተሟጠጠ!

ነጋ ስንል ሲመሽ
ብርሃኑም ሲሸሽ
የደረጀው ሲፈርስ
የሞላውም ሲፈስ
ፈካ፣ አበበ ያልነው … ደርሶ እየረገፈ
                     ዘንድሮም ከነፈ!

እያቀድን ስንቀድ
እየፈታን ስንገምድ
አንዱም ላያ’ዘልቀን
መንታ መንገድ መርጠን
እንዳንደክም’ም ሮጠን
ባዶ አየር ተሞልተን
እንዲሁ ብቻ …
ብር ሽርርር ር … እንዳልን በሰማይ
መስለን የእሳት እራት … ሆነን የእሳት ሲሳይ
ዘመን ተሰወረ … ጨው ሆነና ሟሟ 
               ሊባል ትላንት፣ አምና!

ዳዊት እስቲ ይናገር
ባይዘምር’ ይመስክር
ለምን እንደነበር:
ሰይፍ ታጥቀው
ቀስትንም ገትረው
በሰልፍ አጥቢያ
በዕለተ ውጊያ
*የኤፍሬም ልጆች … የቀሩት ከሜዳ
ያረፈዱት ፍልሚያ?

አቤት የእኛ ትግል
ወጣ ብሎ ከመሀል
ለታዘበው ከዳር
ሲፈተል ላይሾር
ሲዳወር ላይከር
እንዴት … ደስስስ  እንደሚል¡

እኔም ብዙ አልፈትል (አልቅደድ) – መልካም አዲስ አመት!

*የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 77 (78) ቁጥር 9)

Comments are closed.