Post

የዥጉርጉሯ ውሻ ወግ

የዥጉርጉሯ ውሻ ወግ

By Admin

ሰሞኑን “ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ይልቀቁ!” … “የለም! ይህ አሁን መሆን የለበትም!” የሚሉ ድምፆች ተበራክተዋል። እኔም ታዲያ ስልጣን ልታስለቅቃቸው ባትችልም ብትጮህ  – “ብትነክሳቸው” ብዬ ኣንዲት ዥጉርጉር ውሻ ፈጠርኩ …

ዘወትር፦ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ በኣጠቃላይ የብልፅግና አባላት በሚያስብል ደረጃ በየመድረኩ ዲስኩራቸው ነገር ለማሳመር ከነባራዊው ሐቅ ይልቅ ምናባዊ ምሳሌ እየጠቀሱ – ሓሳብ ሲያጠራምሱ ይስተዋላሉ። ለምን? ብዬ ጠይቄ ባላውቅም፥ ምናልባትም አበው ሲተርቱ “ጠጅ በብርሌ – ነገር በምሳሌ” ስለሚሉ ይሆን? ያም ቢሆንኮ  በሁኔታና አድማጭ ይወሰናል። ከነጭ፣ ከቀይና ከጥቁር በሬ ቆዳ በሚገባ በተገመደ የጉማሬ አለንጋ ልቡ እስኪጠፋ ገርፈህ ማስተማር ያለብህን ዋልጌ፣ ነፍሰ-በላ …  “ከዕለታት ኣንድ ቀን … ቀይ፣ ጥቁርና ነጭ በሬ አብረው ይኖሩ ነበር … ጅብ መጥቶ … መጀመሪያ ነጩን፣ ከዛ ቀዩን፣ በመጨረሻም ጥቁሩን በሬ በላ” ብለህ ብትተርት አድማጭህን ታሳምማለህ እንጂ ነገርህን አታሳምርም።

እስቲ እኔም ብትታመሙም “አምላክ ይማራችሁ!” ብዬ ኣንድ ተረት ልፍጠርና የነገሬ በረንዳ ላድርገው። ለወግ ሥርዓቱ እንዳትጨነቁ። እኔ “ተረት ተረት” ስል … እናንተ “ብኣዴን” ማለትም ትችላላችሁ፤ ምክንያቱም፦ በላም-በረት እና በከብት-በረት መካከል ልዩነት ስለሌለ።

ክፍል ኣንድ፦

ተረት ተረት …  ከዕለታት ኣንድ ቀን፦ ኣንድ ነጭ፣ ጥቁርና ጠይም የቆዳ ቀለም ያላቸው ዓይነ-ስውራኖች በኣንዲት ከተማ ውስጥ ኣንድ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር። እነዚህ ሦስት ማየት-የተሳናቸው ግለሰቦች የሚሰሩበት ቦታም አንድ ላይ ስለነበረ፥ ዘወትር ወደ ሥራ ሲሄዱና ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሚያቋርጡት የመኪና ኣውራ ጎዳና ለህይወታቸው ስጋት እንደሆነባቸው ለኣንድ ዓይናማ የጋራ ጓደኛቸው ያጫውቱታል። ይህ ጓደኛቸውም ችግራቸውን እንደ ችግሩ ቆጥሮ፥ ሌላ የሚያውቀውን ግለሰብ አማክሮና ገንዘቡን ከፍሎ ኣንድ guiding (seeing-eye) dog እንዲያስለጥንለት ካደረገ ቦኃላ ውሻውን ይዞ ወደ ዓይነስውራኖቹ ቤት በመሔድ … “እንሆ የስጋታችሁ ዕረፍት! የጓደኝነቴ ስጦታ ነውና ተቀበሉኝ!” ይላል። ሦስቱ ዓይነ-ስውራንም ውሻውን አመስግነው ከተቀበሉና የጋራ ጓደኛቸውን ከሸኙ ቦኃላ ጎረቤታቸውን በመጥራት የውሻውን መልክ (ቀለም) ይጠይቁታል። ጎረቤታቸው የውሻው መልክ ሙሉ ነጭ እንደሆነ ሲነግራቸው፦ ነጩ አይነስውር ሲደሰት ሁለቱ ዓይነ-ስውራን ግን እጅግ በመበሳጨት “ውሻውን አንገለገልበትም፣ እዚህ ቤትም አያድርም! ላመጣው ሰው መመለስ አለበት” ብለው አደሙ። ከብዙ ዱላ-ቀረሽ ጭቅጭቅ ቦኃላ ግን (P.S. ዱላውም የቀረው መገልገያቸው ስለሆነ እንጂ ተደባድበውበት ይሰባብሩት ነበር ) ውሻውን ለባለቤቱ መመለስ የጋራ ጓደኛቸውን ማሳዘን፣ ስጦታውንም መናቅ እንደሆነ በመግባባት “መፍትሔ ነው” ያሉት ኣንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ስለዚህም … ስልጡኑን ነጭ ውሻ …  ጥቁር፣ ነጭና ቡኒ ቀለም ባለው የጎረቤታቸው ውሻ በመቀየር በንጋታው ማልደው፣ የጎረቤታቸውን ውሻ ይዘው ወደ ኣውራ-ጎዳናው ይወጣሉ።

እንግዲህ፦ የቆዳቸውን ቀለም ከህልውናቸው ዓለም ጋር ያስተሳሰሩት ሦስቱ ዓይነ-ስውራን በሰላም ስራ ቦታቸው ይድረሱ ወይንስ የስራቸውን ያግኙ ለማወቅ የእኔን ተረት ክፍል-ሁለት መጠበቅ ሳይሆን  የእናንተን ኢትዮዽያ አሁናዊ እውነታ መመልከት ነው።

ሐቅን ላለማናናቅ፦ ጠቅላይ ሚንስትር ኣብይ አህመድን በተመለከት … ልጓም የሌለው ልወደድ ባይነታቸው፣ የሌላውን ህመምና ስቃይ ፈፅሞ የሚያስረሳ cancerous ግላዊነታቸውና እጅግ ጥልቅ የሆነው መሰሪነታቸው የማስተዳደር ብቃታቸውን ሚዛን ባያሳጣው፥ ተፈጥሯዊ የአመራር ብቃታቸው … ከእርሳቸው በፊት ካየናቸው የኢትዮዽያ መሪዎች ያነሱ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት እንደሌለኝ ሁሉ፤ ከእርሳቸው ቦኃላ ሊኖሩን ከሚችሉ መሪዎችም በላይ የሚያደርጋቸው ልዩ ስጦታ አላቸው ብዬም አላስብም። የዚህ አመለካከቴ መሠረት ደግሞ፦ ሀገር መምራትን ጨምሮ ሌሎች መሰል ሀላፊነትን የሚጠይቁ ተግባራትን ለመከወን ስልጠናና ልምድ እንጂ ተፈጥሯዊ ቁመና የሚኖረው ሚና እጅግ በጣም ውስን ነው ብዬ ሰለማምን ነው።

ለሰው ልጅ እጅግ የቀረበው እንስሳም ቢሆን የኣካሉ መጠን (ማነስና ትልቀት) ለተገልጋዩ “ምርጫ” ሆኖ ሊቀርብ ይችላል እንጂ የየትኛውም ዘር ስሪት (breed type) መሆኑ የተዋጣለት guiding dog ሆኖ ለመሰልጠን እንቅፋት አይሆንበትም። እናም፦ ከዚህ ህሳቤ በመነሳት፦ ኣንዳንዶች  … “በዚህ ወቅት ከዶ/ር ኣብይ አህመድ  የተሻለ መሪ ማግኘት ይከብዳል” የሚሉትን አባባል በፍፁም አልስማማበትም። ባይሆን፦ “መሪ” ሳይሆን “መሐል ሰፋሪ” ቢባል ምናልባትም የማሰቢያ ጊዜ እንኳን ሳልጠይቅ እስማማ ነበር።

እንኳን በራሱ የህይወት ዛቢያ ሲሽከረከር ውሎ ለሚያድረው ዲያስፖራ ቀርቶ፥ እዛው ሀገር ውስጥ ሲንከላወስ አቧራ ቅሞ መርቅኖ  ለሚያመሸው ዜጋም እንኳ ቢሆን … ከስልጣን በፊት የነበራቸው መልክም ሆነ ዝና እምብዛም የማይታወቀው ጠቅላይ ሚንስትር “ወደ ስልጣኑ ማማ እንዴት መጡ?” ብለን ብንጠይቅ …  “በተሻለ ልምድና ተሰጥዖ” የሚል አካል ካለ እንደ ብኣዴን በድን መሆን አለበት። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሌላው ገዝፈው ለዚህ መንበር ጐልተው እንዲታዩ ያደረጋቸው መነፅር ውቅር፦ ጎሳዊ lens ፣ ሀይማኖታዊ frame  እንጂ አስተዳደራዊ ብሌን አልነበረም።

ይህ እውነት ለማንም የተሰወረ ባይሆንም፥  ለመንደርደር ያህል ግን ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት፦  የዘር እና የኃይማኖት ልዩነትን ጫፍ ረግጦ፥  ሰው ለሰው ከማጋደል ባሻገር ሀገር ለማፍረስ ፍጥጫ ላይ የነበረው ፖለቲካችን የዛሬውን ጠቅላይ ሚንስትር ያለምንም ቅድመ-ሁኔታና ምርጫ “አሹ!” ብለን እንድንቀበላቸው አድርጐናል። ለምን?  ቢባል፦ ዘር ላናወዘው ምሁርም ሆነ ሥራ-አጥ … ሰውየው “ኦሮሞ”ም ብቻ ሳይሆኑ ከ”ኣማራ”ም ተወልደዋል። አለፍ ሲልም፦ ምላሳቸው የኣደይ ሮማንን ሚጥሚጣ በሚገባ ያጣጣመ ብቻ ሳይሆን የወይ-ዘሮዋንም ቋንቋ – ትግርኛን – ጭምር አቀላጥፎ ይናገራል። ከዘር  ጠርዝ  ዘለን ወደ ሀይማኖት ጫፍ ስንወነጨፍ ደግሞ፦ ግለሰቡ ከ”ሙስሊም” ቤተሰብ  እንደመገኘታቸው መጠን “ድምፃችን ይሰማ!” ለሚለው ማህበረሰብ ጆሮ መስጠታቸው በሚገባ ታምኖበት ነበር። ይህ ብቻም አይደለም፤ እኔ ባልወድላቸውም አንዳንዴ “አንጀት ለመብላት” በሚመስል መልኩ (ህዝቡ ረሐብ ጠብሶት ጅማት እንጂ ምን የሚበላ አንጀት አለው እንዳትሉኝ እንጂ)  ስልምልም የሚያደርጉት ዓይናቸው … ከማደሪያቸው አጠገብ ከተዘረጋው የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ባሻገር፥ ድንበር አቋርጦ የተሰደደውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶንም ክንፍ ለመመልከት መቻሉ  ሌላ ተስፋ ነበር። መች በዚህ አበቃ? እንደ አባ ገዳ ሰንበቶ የኣደባባይ ምስክርነት ከሆነ … እሬቻን የሚከተለው “ልጅ አዋቂ ሁሉ በየቤቱ የሳለውን ካራ ወደ አልጋው ራስጌ መልሶ ተመቻችቶ የተኛው” የጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት መፅደቁን ከሰማ ቦኃላ ነው። ሌላ “ተገፋሁ” ብሎ እንዳኮረፈ የቀረ ማንን ረሳሁ? አዎ … እጅግ ሰልጥኖ “ኣባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር …” የሚለውን ፀሎት ሳይቀር በጭብጨባና ሽብሽባ ለሚፀልየው ዘመነኛው ፔንጤም ቢሆን የፍቅር ልብ እንዳልነፈጉ በሚስታቸው በኩል በሚገባ አስመስክረዋል፤ አጋፔም ባይሆን “አጋቢ” ፍቅር ሰንቀው ማለቴ ነው።

ብቻ በኣጠቃላይ፦ ሰውየው የሀገሪቱን የዘርና የኃይማኖት ስልጣን ረሀብ ለማጥገብ የተከሸኑ ሚስቶ ሆነው ገበታው ላይ እንደቀረቡ ሁሉም እጁን ለመታጠብ  እንኳን ጊዜ ሳያጠፋ ቆርሶ ጎረሳቸው። ታዲያሳ? ለሙስሊሙም ሆነ  ክርስቲያኑ፣ ለኦሮሞውም ሆነ ለኣማራው ወይም ለትግሬው  ከዚህ በልይ “all in one” dish ማን ያዘጋጃል? ይምረሩ ወይ ይጣፍጡ ሳይታወቅ፣ ጥርስ ያለውም የሌለውም ኣንድ ሆኖ ያለቡራኬ ሳያላምጥ ዋጣቸው …  አሁን እንዲህ ሊተፋቸው።  እሳቸውስ መቼ እንዲህ በዋዛ የሚተፉ ሆኑና! ለምንና እንዴት እንደተዋጡ በሚገባ ስለሚያውቁ፥ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ስራይ ሆነው እስኪዋሃዱ ድረስ ህዝብ በዘር፣ በኃይማኖት ተቧድኖ መደማማት፣ መገዳደል መቀጠል አለበት። ባላገሩ ቢያልቅ Biden አይክፋው እንጂ እሳቸው ምን ተዕዳቸው? ቢበዛ ለጥላ የሚሆን ዛፍ መትከል ነው።

ከኣመታት በፊት ሙሴን ተመስለው መሐል አዲስ አበባ የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ህዝብ ያስጨበጣቸውን የሥልጣን በትር ወርውረው የሰንደቅ ጦር፣ የመዝሙር ካራ አንስተው ውህዱን ማህበረሰብ ከውስጥ ወደ ውጭ  እየበለቱት ነው። ገና ወደ እሳቱ ያልተወረወረው አዲስ-አበቤም ዛሬን በሰላም ስላደረ የተማረ መስሎታል …  ለነገ marinated እየተደረገ እንደሆነ አልገባውም። በዘርና በሀይማኖት ጨረር የታወረች ሀገር፥  በስልጡን ሳይሆን በዥጉርጉር guiding dog እንደተመሩት ዓይነ-ስውራን ሞት ኣፋፍ ላይ ደርሳለች።

ማጅራት መቺ ጨለማ ውስጥ አድብቶ ክፉ ድርጊቱን ሲያጣፍጥ፦ “በለው! ማን አምሽ አለው?!” ይላል። አዎ …  በለው! ማን ምረጥ አለው?!

Comments are closed.