Post

የገና-ዛፍ እና ብልፅግና

የገና-ዛፍ እና ብልፅግና

By Admin

ለኣጭር ቀናት የመስክ ስራ ወጥቼ በተመለስኩ ማግስት ገና ቢሮዬ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ጠረፔዛዬ ላይ ያለው ስልክ አቃጨለ። አነሳሁት፤ በወቅቱ  የመስሪያ ቤታችን ስራ-አስኪያጅና የቅርብ አለቃዬ የነበረው ሰው ነበር። ለጉዳይ እንደሚፈልገኝ ስለነገረኝ ወደ ቢሮው ሳመራ፥ ኣንደኛ ጸሐፊዋ ሀዘን በተሞላበት ፊት ሰላምታ ሰጥታኝ፥ ሰው እንደሌለና መግባት እንደምችል ነገረችኝ። ፊቷ ላይ ባነበብኩት የስሜት ሆሄያት ግራ በመጋባት በሩን ከፍቼ እንደገባሁ፥ በዶክተሩ ግብዣ ተቀመጥኩና ለቀናት ስለሰነበትኩበት ሥራና መንገድ ትንሽ አወራን።

የቅጣትም ሆነ የሥራ-ስንብት ደብዳቤ ሊደርሰኝ እንዳልሆነ በሚገባ ባውቅም ፀሐፊዋ ፊት ላይ ባነበብኩት የሐዘን ድባብ  ግን ሓሳብ ላይ እንዳለሁ ፥ “አዝናለሁ” አለኝ አለቃዬ … የተፈለኩበትን ጉዳይ ሊያስረዳኝ።  ከሁለት ቀናት በፊት ፖሊሶች ነን የሚሉ ግለሰቦች መሥሪያ ቤት ድረስ በመምጣት ያለምንም ምክንያታዊ ቅድመ-መጠየቂያ የቅጥር ፋይሌን ከመዝገብ ቤት በማስወጣት የሚፈልጉትን ወረቀት ኮፒ በማድረግ እንደወሰዱና፥ ስመለስም በመስሪያ ቤቱ ወይንም በመኖሪያ ቤቴ ወረዳ ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት እንዳደርግ እንደታዘዝኩ ነገረኝ። በወቅቱ የተለማመድኩት ክስተት ስለነበረ ብዙ ባልጨነቅም፥  ምን ማድረግ እንዳለብኝ በማሰብ ላይ እንዳለሁ …  “ከፈለክ  እኔም አብሬህ መሔድ እችላለሁ” አለኝ አለቃዬ ። ላቀረበልኝ መልካም ዕርዳታ አመስግኜ፥ መሐል ላይ ሌላ ነገር ካልተከሰተ በስተቀር በቅድሚያ ወደ መኖሪያ ቤቴ መሔድ እንደምፈልግ ነግሬው ከቢሮው ወጥተን ኮሪደር ላይ ስንለያይ … “ስም የሌለው ግለሰብ” አልኩ ለራሴ።

ያኔ … ስልጣን ከመጠን አልፎ ቁንጣን የሆነባቸው ሰዎች፦ ከአክራሪ እስከ የቀድሞ-ሥርዓት-ናፋቂ፣ ከነፍጠኛ እስከ ብሔርተኛ፣ ያሻቸውን ስም ይሰጡን በነበረበት ወቅት አብዛኞቻችን ስም አልባ ግለሰብ የሆንን መስሎ ይሰማን ነበር። የተሻለ ቀን ስንመኝና ለለውጥ ስንፍጨረጨር ይኸው ዛሬ … ገና ሲጠራ ኣፋችንን በሚያሰክር ምራቅ  የሚሞላ ህልውና-የለሽ “ስም” ብቻ የተላበስንበት ኡደት ውስጥ ገባን። ለኣንዱ ብሔር ደህንነት ሌላው መስዋዕት መሆን ያለበት ይመስል፦ “ኦሮሞ” ነህ ግባ፥ “ኣማራ” ነህ ውጣ፤ “ጉራጌ” ነህ ታሰር፥ “ትግሬ” ነህ ተፈታ እየተባለ፥ ለስም ብቻ “የብሔር-ብሔረሰቦች” ቀን “በድምቀት” ይከበራል። ከወታደራዊ ማዕረግ እስከ ቅፅል ሥም፣ ከድርጅታዊ ግብ እስከ ሀገራዊ ትልም  …  ፊልድ-ማርሻልድል-ቁርሱብልፅግናየከፍታ ማማ ወዘተ የሚል፥ ለምላስ  የሚጣፍጥ ጥራጥሬ የተሞላ ሌማት እየዞረ … ያሻንን  ዘግነን እየቆረጠምን … እንዲሁ ሳንጠግብ ሆዳችን ብቻ ተወጥሮ አየርአየር  ሆነን ቀርተናል።

መቼም … ይህ የ TikTok ትውልድ Tricky Talk በቀላሉ ይገባዋል ብሎ ማሰብ ስለሚከብድ፥ የተነፋው ሆዳችሁንም ባይሆን የነገሬን ጭብጥ፥ እየቀረበ ባለው የገና በዓል ልምድ ትንሽ ልበትነው።

እርግጥ ነው … ገና ወይንም የረንጆቹ Christmas  ወቅት  ይመስጠኛል። በተለይም ደግሞ  እንዲህ ጨለማና በረዶ ተዋዶ ውሎ በሚያድርበት ክረምት፦ በየመንገዱ፣ መኖሪያ ቤት መስኮቱ፣ ግድግዳና አጥሩ ላይ ተንጠልጥሎ ብልጭ ድርግም የሚለው የተለያየ ቀለማት ያለው መብራት ምድርን ብቻ ሳይሆን ሙድንም (mood) ያፈካል። እናም …  እንደወትሮው ሁሉ ዓውደ-ዓመቱን ታኮ፦ የጥድ ቅርጫፍ ቆርጠን በየቤታችን አስገብተን የምናስጌጠው የገና-ዛፍ ኣንድ ነገር እንድታዘብ አደረገኝ።

ዛፍን “ዛፍ” ከሚያስብለው መሠረታዊ ባህሪያቶቹ መካከል፦ “ህያው” መሆኑ ብቻ ሳይሆን “ሥር“ ማብቀሉም ጭምር ሆኖ ሳለ፥ ህይወት-አልባና ሥር-የለሹ ቅርንጫፍ “ዛፍ” የመባሉ አግባብ ብልፅግናዊ አስተምሮት ነው፤ የሌለውን – እንዳለ ማሰብ፣ ያልሆነውን – እንደሆነ አግዝፎ መፎገር።

በእርግጥ እንደ ሀገር ኢትዮዽያ፥ እንደ ህዝብ ደግሞ ተረኛ ያልሆነው ኢትዮዽያዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ድርጅት … ስልጠና፣ ድግስ፣ አበባና መብራት ኣራቱ የመቆሚያ ማዕዘናት (pillars) የሆኑት ብልፅግና እራሱ በገና-ዛፍ ይመሰላል። በየማዕዘናቱ የተወጠረበትን artificial ድጋፍ ሳያስተውል ከውጭ ሆኖ ለተመለከተው፦ ሥር-አልባው ብልፅግናም ልክ እንደ “ገና-ዛፍ” ቀጥ ብሎ ሰለቆመ ተተክሎ የበቀለ፣  ልምላሜውም  ገና ስላልጠፋ ህያው ሆኖ የሚፋፋ ይመስላል። እውነታው ግን ብአዴንም በሉት ኦህዴድ፣ ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ፣ ማናቸውም ቢሆኑ … ለወቅታዊ ጥቅምና ጊዜያዊ ደህንነት ድጋፍ ሆነውት የቆመ እንጂ ከግንዱ ጋር የሚያስተሳስራቸው ሥር ቀርቶ ክር የለም። በሌላ አገላለፅ፦ ለግለሰባዊ ብልፅግና የሴራ ድጋፍ ሰጪዎች እንጂ፥ ለፓርቲው ህልውና የሥር-መሰል አገልግሎት አቅራቢዎች አይደሉም። ህወሃትን የከርሞ ድርጅት ያድርጋት እንጂ፦ ብልፅግና ልክ እንደ “ገና-ዛፍ” ሺህ ጊዜ ቢብለጨለጭ … እንደ ብል ከውስጥ ወደ ውጭ በልታ በቁሙ ታደርቀዋለች።

የብልፅግና መሠረት ለጠቅላዩ እንጂ “መደመር”፥  ለጠቅላላው ባለሥልጣን “ማዕድ” ነው። በዚህ የማትስማሙ ከሆነ፦  የላቀ ትምህርት፣ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂንና ማህበረሰባዊ ደህንነትን “ደህና ሰንብት!” ብለው … “የኢትዮዽያ ብልፅግና የሚረጋገጠው በየቤቱ የተትረፈረፈ ማዕድ ሲኖር ነው” ያሉትን ዶ/ር ይልቃል ከፍያለን ሞግቱዋቸው። እኔ ግን ዜናውን ከሁለት ቀናት በፊት ETV ላይ ሰምቼ … “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” ብዬ ተስማምቻለሁ። የህወሃትን ማንሰራራት በመመልከት  የአቶ አገኘሁ ተሻገር መንሸራተትና “ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮዽያ ለብሔር-ብሔረሰቦች ገነት ነበረች” ለማለት መዳዳት፥ የኣፍ-ወለምታ ወይም የምላስ-ስብራት መስሎ ከታያችሁ … አንድዬ ማስተዋል ይስጣችሁ።

ከወረዳ እስከ ቤተመንግስቱ ጓዳ ያለው ባለሥልጣን … ልክ እንደ “ገና-ዛፍ” ቸኮሌትና ከረሜላ እራሱን በቀጭን ክር  በምክንያት ያነጠለጠለ ጌጥ (fake) እንጂ በፓርቲው አስተምሮት የበቀለ ፍሬ አይደለም። በኣጠቃላይ ሊያስብል በሚያስችል ደረጃ … የዚህ መንግሥት አገልጋዮች፦ “ብልፅግናን” እንደፓርቲያቸው አይደለም፥ ኢትዮዽያንም እንደ ሀገራቸው ለመመልከት እጅግ የሚቸገሩ ናቸው። ስለዚህም ነው … የአባት ሳይሆን የኣብይ ቤት የሚዘረፍ እስኪመስል ድረስ ነጠቃና ሙስናው ከመንግስት ቢሮ አልፎ እግዜር ደጃፍ የደረሰው። ለነገሩ … በእነርሱ ማን ይፈርዳል? ኢትዮዽያ እንደሆነች … ለጠቅላይ ሚንስትሩ … ከቤታቸውም በታች አንሳ ጠባለች። ዕለት-ተዕለት በማን-አለብኝነት በሀገሪቷ ህልውና እና በህዝቦቿ ላይ በተናጥል የሚወስዱት እርምጃ፥ በቤታቸውና በአጥንታቸው ክፋይ ላይ እንኳ እንዳይሞክሩት ህግ የሚያግዳቸውን ወንጀል ነው። ታዲያ፦ የዘመኑ ተረኛ  … ሀገርን እንዲህ አሳንሶ፦ “የኣባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለውን ተረት … የኣብይ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ … በሚል ሐረግ ቢተካው ማን “ተሳስተሀል!” ይለዋል?

Comments are closed.