Post

የፕሪቶሪያው ሰንሰለት

የፕሪቶሪያው ሰንሰለት

By Admin

ለማንበብም ሆነ ለመስማት ስልችት ያለኝ ነገር ቢኖር “የፕሪቶሪያው ስምምነት” የሚለው ሐረግ ነው። ለትንሹም ለትልቁም – ለወፍራሙም ለቀጭኑም ጉዳይ “የ Pretoria agreement” እያሉ ማላዘን። ምርጫ ቦርድ፦ ‘ህወሃትን ዳግም በፖለቲካ ፓርቲነት አልመዘግብም’ ሲል … ”የፕሪቶሪያው ስምምነት!”  ብሎ መጮኽ። ትምህርት ሚንስትር፦ ‘ወልቃይትና ራያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔት በኣማራ ክልል አስተዳደር ስር ናቸው’ የሚል  assessement report ሲያወጣ … ”የፕሪቶሪያው ስምምነት!” ብሎ ኡ! ኡ! ማለት። ይህ ጉዳይ በዚህ ከቀጠለ … ነገ … በዚያ መንደር በትዳር ፍቺ ላይም የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይጠቀስ የሚቀር አይመስለኝም።

ህወሃት፦ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ መከራ ሲያዘንብ ሁለት ትውልድ ማምከኑ ሳያንስ ዛሬም እንደ ስለት ልጅ ሸምናችሁ አልብሱኝ፣ ሸምታችሁ አጉርሱኝ ሲል በረባ ባልረባው ያለቅሳል። ለነገሩ … “የማይገርፉት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል“ አይደል የሚባለው። ይህ የመርገምት ቋት ኣራት ኪሎ ከመግባቱ በፊትና ከገባ ቦኃላ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያኖች ላይ ያወረደውን በላ ወደ ጎን ትተን፤ ከኣራት ኪሎ ከወጣ እና የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ቦኃላ ያሉትን ጥቂት ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት እንኳ፥ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ላይ ያደረሰው አካላዊ፣ ስነለቦናዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደ ቀላል በእርቅ የሚታለፍ አልነበረም። ግን ምን ዋጋ አለው … ልፍስፍስ መሪ ከእራሱ አልፎ ሀገር ያልፈሰፍሳል።  

ከሁሉ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ “የሌባ ዓይነ-ደረቅ …” እንዲሉ ገድለው – ተገዳይ፣ ዘርፈው – ተዘራፊ፣ በድለው – ተበዳይ ሆነው ‘የተለየ ጥቅምና አገልግሎት ይሰጠን!’ እያሉ መጮሃቸው ነው።  

ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት በቅጥረኝነት ቀስቅሰው የሀገሪቷን ሰዋዊና ቁሳዊ ቅሪት ዶግ አመድ በማድረግ ሀገርና ህዝብን በኣሥርት ዓመታት ወደኋላ በመመለሳቸው ካሳ መክፈል ሲገባቸው፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዜጋ ነፍስ በከንቱ እንዲጠፋና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሲቪሊያን ከቅዬያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት በመሆናቸው በሕግም ሆነ በታሪክ በወንጀለኛነት መጠየቅ ሲኖርባቸው … ጭራሽ እነርሱ ተበዳይ፣ እነርሱ ተጎጂ፣ እነርሱ ከሳሽ ሆነው ከሀገር ሀብት ላይ “ከባንኮች የተበደርነው እዳ ይሰረዝ፣ መሽገን የተታኮስንባቸው ቤተክሪስቲያኖች፣ ትምህርት ቤቶችና የኢንዱስትሪ ተቋማት በአስቸኳይ ይጠገኑ፣ ተፈናቃዮች  በቀናት እድሜ ወደ ‘ቅዬያቸው’ ይመልሱ እያሉ የሰው ጩኸት በመቀማት “የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጣሰ! ሲሉ ላንቃቸውን ይቀዳሉ። ይህ በየትኛውም መመዘኛ ብልግና እንጂ ብልጠት፣ ወያኔነት እንጂ ወኔያምነት አይሆንም።

ህወሃት፦ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ሊገመቱ የሚችሉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀብት የሆኑ ወታደራዊ መሳሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን በምርኮና በውርስ ድንበር አልፈው እንዲወሰዱ ምክንያት ሆኗል።  ባለፉት ጥቂት ዓመታት፦ በድርድርና በሰበብ አስባቡ መቀሌ እያረፉ በሚነሱት አይሮፕላኖች በርካታ የወርቅና የውጭ ምንዛሪ ሻንጣዎችን በኣደራና በስጦታ ከሀገርና ከህዝብ ሰርቆ አሽሽቷል። እነዚህ ኣይሮፕላኖች መሬት ለቀው ሊበሩ የቻሉት በኣምላክ ሚስጢር እንጂ እንደተጫኑት የሀገርና የህዝብ ንብረት ክብደት ቢሆን ኑሮ ከመቀሌ እስከ ጅቡቲና ናይሮቢ በረው ሳይሆን እንደ ባቡር ምድር ለምድር ተስበው በደረሱ ነበር። የመንግስታቱ ድርጅት አለቃ “ትግራይ እንዳልሄድ ተከለከልኩ ሲሉ ያኮረፉት፥ መቀሌ ውስጥ ዓይኑን ለማየት የናፈቁት ቤተሰብ ኖሯቸው ሳይሆን ሊጨብጡት ያሰቡት ወርቅና ዶላር አጓጉቷቸው ነው።

ይህ ሁሉ ወንጀልና ክህደት በሀገርና በዜጎች ሀብት ላይ ተፈፅሞ እያለ፥ ህወሃትና ደጋፊዎቹ ጩኸታችንን በመቀማት የሚያለቅሱት ስላማረኩብን ስፍር ቁጥር የሌለው ተተኳሽ፣ ስላስወረሱን surface to air missiles፣ ስላሸሹት ወርቅና የውጭ ምንዛሪ ሳይሆን ስለ ማንኪያና ሹካ፣ ስለ ባዶ የወሃ ጄሪካን ነው።

እውነት ለመናገር፦ በፕሪቶሪያው ስምምነትም ሆነ በፕራዮሪቲ (priority) መርሕ … ህወሃት “ጠያቂ” ሳይሆን “ተጠያቂ” መሆን የሚገባው ሀገርና ህዝብን ያደኸየ ቅጥረኛ አካል ነበር። ግን ምን ያደርጋል፦  “አንቺ ምን አደረግሽ ሰው ነው ያጠፋሽ … ተኚ ተኚ እያሉ ሳያንቀላፋሽ” ነው ያለው ዘፋኙ? በእኔ እምነት የፕሪቶሪያው agreement ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያኖች “ስምምነት” ሳይሆን ዳግም የመከራ ሰንሰለት ነው።

*Original feature image credited for unknown artist

Comments are closed.