Post

ያንን ቀጨን ኩታ ጣል አድርጌ

ያንን ቀጨን ኩታ ጣል አድርጌ

By Admin

የዘንድሮ ምርጫ እንደ ከፍተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የሚታረም እንጂ የሚቆጠር አይመስልም። ድምር ውጤቱን ለማወቅ ይኸው ቀናት ተራብተው ሳምንታትን ወልደዋል። “ምነው? ጓጓህ እንዴ?” ብባል፡ መልሴ ላለመዋሸት “አዎን” ነው፦ ለማውቅ ባይሆን ለመሳቅ

ለሚቀጥሉት ኣመስት ዓመታት … ?

እንደው ይህን ወሬ የወያኔ ጆሮ አይስማውና፡ ተቃዋሚዎች “ያልተቆጠረውን” 105 ወንበር (ሃያ ፐርሰንታይል) አሸነፉ ቢባል፡ ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? ስል ዛሬ ጠየኩ። የትግላችን ቁም-ነገር ከወንበሩ ቁጥር ጋር ሳይሆን ከነፃነት፣ ከፍትህና እኩልነት ጋር እንደሆነ ሀቅ ነው። ሙታን ህያዋንን በወከሉበት በድን ምክር-ቤት ውስጥ የተቃዋሚውን ቁጥር ከኣንድ ወደ ኣንድ-መቶ-ኣምስት በማሳደግ፡ በደል፣ እስር፣ ግድያ፣ ዘረፋና ዘረኝነት እንደ ወረርሽኝ ተንሰራፍቶባት፡ ከጓዳና ተዳዳሪው እስከ አይሮፕላን አብራሪው ሀገር ጥሎ የሚሰደድባትን ምድር መታደግ እንደማይቻል በሚገባ አውቃለሁ።

እናስ? ወያኔ የስልጣን ልጓሙን ጨብጦ በሚኖረው ቀጣይ የኣምስት ዓመታት ጉዞ፡ የሀገር ሃብት በትውልድ ለእነ ተዎልደ፥ የህዝብ አርነት በዘር ለእነ አርአያ ዘሪሁን ተከልሎ – ተወስኖ፡ ሲመዘበር – ሲተገበር፡ ያለ ቁጭት የሚመለከት ዓይን፣ የሚያዳምጥ ጆሮ ይኖረናል? ለሚቀጥሉት ኣምስት ዓመታት፡ የወያኔን የስልጣን ኮርቻ፣ የዘረኞችን ቀንበር የሚሸከም ያልተላጠ ጀርባ – ያልጎበጠ ትከሻ አለን? ለሚቀጥሉት ኣመስት ዓመታት ለእስር- ለካቴና የተዘጋጀ እጅ፣ ለበረሃ- ለስደት የሚሆን ጉልበት፣ ለአደባባይ ግድያ የሚውል ነፍስ፣ በግፍ የሚፈስ ደም ይኖረናል? መልሱ ግልፅ ነው።

ወያኔ በህፃን አእመሮው የተጫወተውን የልጆች ጨዋታ (ምርጫ)፡ እኛም በልጆች ቋንቋና ለዛ “እፍርታም!” ብቻ ብለን፡ ውጤቱን ተቀብለን፡ በተሰጠንን ወንበር እጆቻችንን አጣምረን አርፈን አንደማንቀመጥ ሰምና ወርቅ የሌለው ቃል ነው። እንደ ጀንበር- ጨረቃ፡ የነፃነት ውበቱ ሙሉነቱ ነው። ከተሸረፈ አርነት፡ ሙሉ ባርነት ይሻላል፥ ለዓመፅ እና ለትግል ያነሳሳል።

በሳሪያን ኮት ላይ … ያንን ቀጨን ኩታ ጣል አድርጌ

የዚህ ጽሁፍ ርዕስም ሆነ በማስቀጠል የምጠቀመው የዘፈን ሐረግ፡ ከግጥሙ ደራሲም ሆነ ከድምፃዊው ግለሰባዊ ትርጉም ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ መስተሳስር እንደሌለው ማሳሰብ እወዳለሁ። ሆኖም ግን፥ ህያው ነፍስ ያለበት የወንድሙ ገላ እንደ ደረቅ ከሴ ነዶ ሲከስል እየተመለከተ፡ ዛሬም ሀቅን ለመናገር የሚሳቀቅ፣ እውነትን ለማንበብ የሚሸማቀቅ ” ዜጋ ” ካለ፡ ርዕዮት ዓለሙ የቃሊቲን ቱታ ስትጣጠቅ ያወለቀችውን ቀሚስ ይልበስ እላለሁ።

ወደ ዋናው የጽሁፌ ሀሳብ ስሳብ፦ አሁን ላለው መንግስት የሃያ-ሶስት ዓመታት የስልጣን ዘመን ስሌት ትልቁ ብዜት የተቃዋሚዎች ህብረት ማጣት እንደሆነ አያካክደንም። ለለውጥ ተግባራዊነት የምንገነባው የተቃዋሚው ድክመት እንጂ የምናፈርሰው የወያኔ ጥንካሬ ስለሌለ ነው፡ ተቃዋሚውን- በተለይም ከሃገር ውጪ ያለውን “የለውጥ ሀይል” በቀና መንፈስ ለዕርምት የምንተቸው፤ ልዩነታችን ሰፍቶ ኣንድ መሆን ቢቸግረን እንኳን ህብረት ይኑረን የምንለው። የዘር፣ የሀይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነታችንን በኣንድ ሰንደቅ-ዓላማ ስር አሰባስበን፡ ህዝቡን ለሀገራዊ እምቢተኝነትን ማነሳሳት ከቻልን፥ ፍርሀት እንጂ ጠመንጃ ህዝብን የገዛበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ የለምና፡ ከአደባባይ የሚያርቀን ኣግ-አዚ፣ ከድል የሚያቆመን አምባገነናዊ አገዛዝ አይኖርም!

ሞልቶ በኣራዳ የአርመን ዳቦ … ሳሳ ገላዪ ሰው ተርቦ

ፖለቲካዊ ትግል ከራስ ወዳድነት ፍጹም የፀዳ ሊሆን ይገባዋል። የአመራር ራዕይ ሚዛን የሚደፋው፡ የግቢውን ሙላት ሳይሆን የማዶውን ጉድለት፥ የራስን በረከት ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ማጣት መመልከት ሲያስችል ነው። መስዋዕትነት ግዙፍ ዋጋ የሚኖረው፡ መከራና ስቃይ ገፍቶ መጥቶ የራስን ጓዳ ሲንድ ሳይሆን፡ ገና የጎረቤትን ደጃፍ ሲያንኳኳ ተመልክቶ በዝምታ ማለፍ ሳያስችል ሲቀር ነው። ጠግቦ በልቶ ሰው ተርቦ ሲመለከት የሚከሳ፥ በንጉስ እልፍኝ ተቀምጦ በባርነት ለሚድሁት የሚቆረቆር፡ ያ ሰው፡ እንደ ሙሴ ክብርም በትረ-አሮንም ይገባዋል።

የእኛስ መሪዎች? ለህዝቡ ያላቸው ፖለቲካዊ መክሊት ምንድነው? የራዕያቸው፣ የመስዋዕትነታችውና የተቆርቋሪነታቸው ፍሬ ግለሰባዊ ነው ድርጅታዊ? ወይንስ ሀገራዊ? ትላንት አንደ ጵላት የገዘፈ የኮሚኒስት ማኒፌስቶ ታቅፈው፡ ድርሰቱን ሳይሆን ደራሲውን የተሸከሙ እስኪመስሉ ድረስ ጎብጠው በየመንደሩ የሚንጎራደዱትን ሊቅ-መሰል የአኢወማ ሊቃነመናብርት አስታወሼ፡ ዛሬ ላይ በሽመል ኣሊያም በሸክም ካለሆነ የቢሮቸውን ሦስት ደረጃ መውጣት የማይችሉትን የድርጅት መሪዎች ስመለከት፡ ፖለቲካችን ዕድገቱ፦ ከጉራ ወደ የማታ እንጀራ ሆኖ እንዳይቀር እፈራለሁ።

እንደ ኣውራ ዶሮ ክንፍ … ኮቴን እየሳብኩት መሬት ለመሬት
በዞርኩት ገላሽን … ሳትወጣብኝ ፀሀይ ሳይነጋብኝ ሌት

ድርጅታዊ የስልጣን ማዕረግን፡ እንደ መጠሪያ ስም ከልደት አስከ ሞት “ይገባናል” ብለው፡ ከወዲያኛው ትግል እስከ ወዲህኛው ፍልሚያ የዘለቁት “ፋኖዎች” የዚህን ትውልድ የፍላጎት ውሃ-ልክ ሊያወቁት፡ አለበለዚያም አመራሩንም ሊያስረክቡት ይገባል ብለን ስንል፡ ውለታ ቢሶች ሆነን፣ ትላንት ለከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ዋጋ ሳንሰጥ ቀርተን አይደለም። ነገር ግን፦ ህይወት ነውና፡ ለውጥ አይቀሬ ሆኖ የዘንደሮው ፖለቲካዊ ፍቅርም ሆነ ፀብ ከአምናው ፍጹም የተለየ አቀራረብ፣ አያያዝ እና መስተዳድር ስለሚያስፈልገው ነው። ጥሎን የነጎደውን ዓለም-አቀፋዊ መብት እና ስልጣኔ፡ ሃዲድ እና ባቡሩን ቀይረን በተሻለ ፍጥነት ሳይረፍድ- ሳንዘገይ ከነገ ላይ መድረስ እንፈልጋለን ስንል፥ ከትላንት ዛሬ ላይ ላመጣን የከሰል ባቡር ንቀት አድሮብንም አይደለም። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፡ ሃገራችንና ህዝባችን ላይ ያጠላው የጥፋት ደመና ጊዜና ፋታ የማይሰጥ ሆኖብን አንጂ።

ለዚህም ነው፦ የአንዳንድ አመራሮችን ፍትወተ-ስልጣን ስናወግዝ፡ የእኛም ዘገምተኝነት ሃገር የሚያሳጣ የከፋ ትውልዳዊ ሀጢያት እንዳይሆንብን፡ ሳንውል ሳናድር የከፋፋዮችን ዘር-አዊ ከልል አፈር አልብሰን፡ በሃገራዊ ድንበር ልንውጠው ይገባል የምለው። ነፃነትን በጉልበት ለማስከበር፡ ህብረ-ብሔራዊ እምቢተኝነት ብቸኛው አማራጭም ባይሆን፡ አዋጭ የትግል ስልት ነው።

የህዝብን ቁጣ ለማቀዝቀዝ፡ የምርጫን ጠቅላላ ውጤት ማዘግየት ፋይዳ-ቢስ ስነልቦናዊ ጨዋታ ከመሆኑም ባሻገር፡ መንግስት የሚፈራው ሊያስወግደውም ያቀደው የብዙሃኑ ስብስብ፡ በወቅታዊ ቀመርም ሆነ በሀይማኖታዊ ስርዓት (በትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ በረመዳን ጾም፣ ወዘተ ) ሊያሳካው እንደማይችል ማመን ግድ ይላል።

መጣሁ ከኮርያ ይዤልሽ ሰዓት … ይቀጥላል

Comments are closed.