Post

ያ ሰውዬ … ምን አለሽ ማታ?

ያ ሰውዬ … ምን አለሽ ማታ?

By Admin

እረኛው ጠፋና … መንጋው ተበታትኖ
ግልገል ከጠቦቱ … የኣውሬ ጭዳ ሆኖ
የአብረሃም በግ ታርዶ … ሳራ ብትረዳ
አየሁ ኣንድ ተኩላ

ነካሽ … አናካሹ
“ሊያለቅስ” … አስለቃሹ
ቁጭ ብሎ ታድሞ … የሙክት ለምድ ለብሶ
የአዞ ዕንባ አቀርዘዞ …

እግዞ!
ተከፋች ነፍሴ … ተጣላች ከራሴ
ቆጨኝ – አሳፈረኝ … ያ ጅል ልጅነቴ
ማር እቆርጥ ብዬ … ንብ መስሎኝ ታልዬ
ለተርብ ቀፎ ስሰቅል … ልነደፍ – ልቆስል
ልከርም እሾህ ስነቅል

ግና …
ወግ ባህል ነውና
ጥይት አዘግኖ … እርሱም ንፍሮ ዘግኖ
ሲሄድ ተሰናብቶ
“እቴሜቴ … የሎሚ ሽታ
ያ ሰውዬ … ምን አለሽ ማታ?”

ምንም ምንም … ምንም አላለኝ
ልጆቼን ገድሎ … “ነፍስ ይማር አለኝ”
አይቀልድም … ልጆችሽን ገድሎ
ምሎልሻል … ጋሻ ጦር ይዞ!

Comments are closed.