Post

ይኽቺ ናት ቆረጣ!

ይኽቺ ናት ቆረጣ!

By Admin

ለሳምንታት የዘለቀውን የህወሃት (ጥቂቶች “የኢህአዴግ ” ይሉታል) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ስታዘብ ከረምኩና፥ ጀንበር በመጥለቂያዋ ሰዓት፦ “አቶ ደመቀ መኮንን ከጠቅላይ ሚንስትርነት ምርጫ እራሳቸውን አገለሉ፤ ዶ/ር አብይ አህመድም አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ ” የሚለውን ዜና ስሰማ “ይኽቺ ናት ቆረጣ!” አልኩኝ። በድኑ ብአዴን ባነነ!  

በዶ/ር አብይ አህመድ ምርጫ፥ ህወሃት አመድዋ ቡን እንዳለ ባለፈው ሰኞ የህወሃት (“የህዝብ ” ለማለት ስለሚከብድ ነው) ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባን አስመልክቶ የታደምነው ተንቀሳቃሽ ምስል በድምፅም ባይሆን በአካል ቋንቋ (body language) በሚገባ ተርኮልናል። ህወሃት ምኞቷ፦ የእራሷን ድምፅ አስቀድማ፣ ብአዴን እና ደህዴድን ደልላ አቶ ደመቀን በአብላጫ ድምፅ ማስመረጥ፥ ከዚያም ዶ/ር አብይን አሊያም  ኣንድ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ታኮ አስገብታ ስልጣኗን ማቆም ነበር። ብአዴን እና ኦህዴድ ቀድመው ባነው፥  በዚያ “ዴሞክራሲያዊ ” በተባለለት ደም-አልባ ደፈጣ፡ በራስዋ ስልት “ቆረጣ” ከምትወደው ስልጣን አቆራረጥዋት እንጂ። ይኽም ቢሆን ግን እልልል! ለማለት ገና ብዙ እልህ አስጨራሽ መንገድ ይቀራል።

እንደው ልንደረደርበት ፈልጌ እንጂ፥ የዛሬ ርዕሴ የጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫ ሳይሆን ሚንስትሩ እራሳቸው ናቸው። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፡ በውስጥም ይሁን በውጭ ሰፊ ተቀባይነትን ከማግኘታቸውም ባሻገር፥ ከምን በመነሳት እንደሆነ በውል ባይገባኝም፡ በተለይም በሶሻል ሚዲያው ላይ ቀላል ቁጥር የሌለው ሚዲያተኛ ዶ/ር አብይን ከብሉይ ኪዳኑ ሙሴ ጋር እያመሳሰለ ይሰብካቸው ጀምሯል። የተወረስነው ሀገር እና መሬት እንጂ፥ እሳቸው የሚያወርሱን አዲስ ከንዓናዊ ምድር እንዳለ ግን  ለእኔ ገና እንቆቅልሽ ነው። በእርግጥ ዶ/ር አብይ አህመድን’ና አይሁዳዊውን ሙሴ የሚያመሳስል ኣንድ እውነት አለ። ሁለቱም የህዝብ መሪዎች፦ ትውልዳቸውም ባይሆን ዕድገታቸው ጭቆናና ስቃይ መለያው በሆነ ገዢ ቤተሰብ ውስጥ መሆኑ። ኸረ እንዳውም የፈርኦን ቤት ይሻላል ሳያስብል ይቀራል? ቢያንስ እንኳን ስር-ግንዱዋን ተቃውማ፡ ለሙሴ የራራች ኣንድ ሴት ልጅ ተገኝታበታለች።    

የሳይበሩ ዓለም ዶ/ር አብዩን ከነብዩ ጋር ማመሳሰሉ በግብር እና ምግባር እንጂ በመልክ አይደለምና “ኸረ በህግ!” ብሎ ለመሞገት ገና ጠዋት፣ ማለዳ ይመስለኛል። ሚንስትሩ ከተሾሙ ቀናት ተቆጠሩ እንጂ ሳምንት እንኳ አልሞላምና። አንዲያው ግን፥ ዶ/ር አብይ ዙፋናቸው እንድትፀና፣ በሹመታቸው ማግስት የሰበኩን ፍትሐዊ መንግስትም እንድትመጣ ትልቅና ፈታኝ ስራ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው አስታዋሽ የሚፈልጉ መስሎ ባይታየኝም፥ ኣንድ ነገር ለማለት ግን ወደድኩ። አጀማመራቸው እንጂ አፈፃፀማቸው እንደ ሙሴ እንዳይሆን፣ የተስፋይቱን ሀገር በናባው ተራራ ላይ ቆመው ባሻገር ከማየት ውጪ በእግራቸው ሳይረግጡዋት፣ አልፎም ሳይወርሱዋት እንዳይቀሩ፦ በጣም በጣም እጅግ በጣም መጨከን ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ፦ እንኳን በድምፅ ብልጫ፡ በመለኮታዊ ምርጫ የተገኘች መንግስትም ብትሆን ለኣፍታም እንደማትፅና ሊያስተውሉ ይገባል። ብሉይ ኪዳን የሙሴን ገድል ብቻ ሳይሆን የሳኦልንም ዕድል ፈንታ እንዲህ ያስተምራል:   

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ - ምዕራፍ 15: 12-22
ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም– አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው።  ሳሙኤልም– ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና  የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? … በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም  በእስራኤል ላይ  ንጉሥ ትሆን  ዘንድ  ቀባህ። እግዚአብሔርም፦ ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው  ብሎ በመንገድ ላከህ። ለምርኮ ሳስተህ ለምን  የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ? ሳኦልም ሳሙኤልን- … ሕዝቡ ግን  ለአምላክህ  ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ  ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን  በጎችንና  በሬዎችን  ከምርኮው  ወሰዱ  አለው። ሳሙኤልም– … የእግዚአብሔርን ቃል  ንቀሃልና  እግዚአብሔር  ንጉሥ  እንዳትሆን  ናቀህ  አለ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ፡ አለኝ እንዳሉት ራዕይ፦ ዘረኝነትን፣ ቀማኛነትን እና የስልጣን ብልሹነትን ለማጥፋት ሲዘምቱ፡ አንዱን ከሌላው እያበላለጡ፣ በከሱት እና አይን-በማይገቡት ክልላዊ ሙሰኞች ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በመንግስታቸው’ና በስልጣናቸው ዙሪያ በሚያገሱት፣ በሰቡት ዘረኞች እና ቱባ ሀገራዊ ዘራፊዎች ጭምር ላይም ሊሆን ይገባል። የኢትዮዽያ ህዝብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የአምላክም ፈቃድ እንዲሁ ነውና። ይህንን ስል ግን፥ እንደ አማሌቃውያኑ ሁሉ ከማሌሊታውያኑም ጋር የሚደረገው ትንንቅ የሚናቅ እንዳልሆነ ለሁላችንም ግልፅ ነው። መረሳት የሌለብት ሀቅ ግን፦ ዶ/ር አብይ ለዛሬው ስልጣን ብቃት የሆናቸው የኢትዮዽያ ህዝብ አመፅ እንጂ በባህላዊ ግጭትና አፈታት ሂደት ላይ የፃፉት አምድ ወይም ዲዘርቴሽን (dissertation) አይደለም። ብዙ ከፍታ ወደ-ላይ ያወጣቸው የህዝብ ክንድ፥ እሳቸው ኣንድ እርምጃ ወደፊት ሲራመዱ ከተመለከተ፦ በእጥፍ ሊያግዛቸው፣ ተሽክሞም ከተስፋይቱ ምድር ሊያደርሳቸው የቆረጠ ነውና፥ የትኛውንም ጐሳዊ ተቃውሞ፡ በሀገራዊ ድጋፍ መመከትና ማሽነፍ እንደሚችሉ ለኣፍታም መጠራጠር አይኖርባቸውም።

ከዚህ ባሻገር ግን፥ የህወሃት ከፋፋይ ስራይ (በሽታ) በዘር’ና በስሩ ብቻ ሳይሆን በግንዱም የሚራባ ክፉ ነቀርሳ ነውና፡  ጠቅላይ ሚንስትሩ ህወሃትን ብቻ ሳይሆን ግንዱን ኢህአዴግን (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴድንን ጭምር) በዓይነ ቁራኛ መመልከትና ስጋት ሆኖ ሲገኝም ውለው ሳያድሩ ዱላ ሽጉጡን ሁሉ ያለርህራሄ  በጥበብ ማምከን ይኖርባቸዋል

ይሆናል ብዬ ለመገመት ብቸገርም፥ ነገ አስገንጣዮቹ  ካልተገነጠሉ በቀር አሁን ቆራጮቹ ተቆርጠዋል። ህወሃት በአዲስ አበባ እና በተቀረው ክልል እንደ ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እንጂ እንደ ትግራዋይ በበላይነት መኖር እንደማይቻል በሚገባ ተረድታለች። ትላንት በሀገሪቱ መሐል እምብርት ላይ በእምበር ተጋዳላይ ሲዘሉ የነበሩ ዘረኞች፥ ዛሬ ቀስ በቀስ “ለበለጠ ሃላፊነት ” በሚል ሰበብ ወደ ዳር መሳብ እና መሰባሰብስ ለምን ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስም ሆነ በህወሃት ቆረጣ ሳይቆረጥ አስቀድሞ  የመቁረጡን  ተግባር  ለትግራይ  ህዝብ ትቼ ፅሁፌን በዚሁ ላጠቃል። 

Comments are closed.