
By Admin
ጅራቱ ለንቁጦ … ፋይዳ አልባ አካሉ
ቆዳው ቢዥጎረጎር … ላይገጥም የስም ቃሉ
በቀን ቀን ሊያነባ … በምሽት ቅዥቱ
አሻፈረኝ ብሎ … ድመት የማጀቱ
ካልነበርኩኝ ካለ … እንደጫካው ብርቱ
ይጋመዳል ሲሉ … ዘር ድሩ ሲፋተል
ሲጠራ ሲጣቀስ … ከነብር ሲማሰል
በኢምንት ባህሪው … ከቁጡው ሲቃጠል
ድርሻ አለው ሲባል … የቅም ቅማንቱ ውርስ
የአያቱ ኑዛዜ … ዝብርቅ የቆዳ ልብስ
ልቡን አስቆብቁቦት … ጎሮ ዋዩን ውሮ
ዱር ካልገባሁ ካለ … የእኛው ድመት ነብሮ
ቢፈታ፣ ቢለቀቅ … እስቲ ምን አለበት
ድመት ነብር ላይሆን … አጉል ባይሞገት?
አይጥ አይታው ብትሮጥ … ልቡ ትምክህት ቋጥራ
ጫጩት ብትጮህለት … ተነፍቶ በጉራ
ካአለ አሻፈረኝ … በረሃ ሊቃትት
ከዘሩ ተጣልቶ … በዘሩ ሊሸፍት
ነብርን መሆን ሽቶ … የድመት ተላላ
ዱር ካልገባሁ ካለ … አድኖ ሊበላ
ምንድነው ዘራፉ … ሽርጉድ፥ብትኑ
የሰልፉ ጋጋታ … ድምፅ ፣ ሪፈረንደሙ
የአዳም ዘር መድከሙ … ለማጀቱ ድሙ?
በሚዳቋ አጥንት … ሳምባ በዪው ገዝፎ
ፍየል ፈረስ ላያልቅ … በረት ፣ ጋጣ ጥሶ
ቅዥት ራእይ ሆኖ … ጫካ ውሎ ውሮ
ነግሶ ላይመለስ … አውሬ ሆኖ ነብሮ
ወጥመድ አንጀት አልባው … ሞልቶ በከተማው
የጓዳውን ጥሬ … አይጥ ላይቃመው
እስቲ ለምንድነው … እናቲቱ የቆጨሽ
ሂድ ሳትዪው ልሂድ … በቃኝ ፣ ፍቺኝ ሲልሽ?
ዘልቆ ላያዘልቀው … ሲለቀው ቅዥቱ
ደርሶ ውል ሲለው … ሳንባና ወተቱ
የሚታደን ጠፍቶ … ሲበዛ አዳኙ
አይቀር መቼም ደሞ… ይመጣል ቀን ቆጥሮ
ያልነበረው ውሮ … ጭራውን ቀስሮ
እንደ አሞራ በሮ
ታድያሳ ለምን ነው … እንዲህ መጨነቅሽ
በድመቱ መጀን … እናት መለመንሽ
ልቀቂው በሞቴ … ይሂድ በፈጠረሽ
ውሮ ጫካ ነብሮ … እኔም ወጥመድ ልስጥሽ፤
ተክልዬን ልቀቂው … ይሂድ በእስጢፋኖስ
ለቀለብ አይደለ … ያለመድነው ወትሮስ፤
ግን ብቻ ታሪክ ነው … ታሪክ ነው የሚገርም
ተኩላ ሄደ ብሎ … በግ በሃዘን ሲታመም።
1984 ዓ.ም.