ሰኔ እና ሰኞ ነው … ከሰዓት ቦሃላ
ወደ ቤት ሳዘግም … ወጥቼ ከስራ
ፌርማታ ላይ ቆሜ … ባስ ስጠብቅ ሳለሁ
13-ቁጥር መጥታ … ተሳፍሬ ገባሁ፤
ወደፊት ገደማ … ቦታ ስለነበር
ሁላችንም ከፍለን … ለመያዝ ስንል ወንበር
ኣንድ ባላገር መሳይ … ድልብ ባለ ጡንቻ
ሙግት ይሞግታል … ከቲኬት ቆራጯ፦
“ከጅምሩ አልገባሁ … ከወዲያ፣ ከማዞሪያሽ
ከመሃል ሰፍሬ … እንደዚኽ መቸኽሽ
ደግሞም አላቀፍሺኝ … በአንቀልባ አላዘልሺኝ
መኺናው ተንጦ … ቁልቁል በሰደድሺኝ
ትንሽም አታፍሪ … ግፍንም አትፈሪ
ኸዚች ኸዚያች ልሔድ … ሙሉ ሂሳብ ስትጠሪ?”
እያለ ሲናገር … ቁጣንም ጨማምሮ
ለቲኬት ቆራጯ … ግንባሩን ኮስትሮ
ዘለፋው ሲበዛ … ትዕግስቷ ተሟጦ
ሳቋን ገታችና … አንጀቷ ተቃጥሎ፦
“ትሰማለህ ሰውየው … ክፈል ብዪሃለሁ
ከመነሻውም ገባህ … ከመሃል ለውጥ የለው
ሙሉ ሂሳብ ነው ዋጋው … ሰው ሁሉ የሚከፍለው
አሻፈረኝ ካልክም … ባሱን አስቆማለሁ
ታክሲ አደረከው … ቅናሽ የምትለው
የማን ነው ባላገር … እርጥብ የማይገባው“
ብላ ብትል “ኡፍፍፍፍፍ” የኛዋ ዘመናይ … ጭቅጭቅ ሰልችቷት
አካሉን ወጥሮ … አይኑን አፍጥጦባት፦
“ይኽቺን ይወዳል … ኸረግ ደምስሳቸው!
እንግዲያ ጥሪዋ … እስቲ በይ ባሱ ይምጣ
ኸንኳን ብታስቆሚው … ቢዘልም አልነጣ
ሳዱላ አደረግሺኝ … ተጣልቄ ቁምጣ?”
ብሎ አማተበና … መዳፉን ቆጣጥሮ
ቢልብን ገልመጥምጥ … የቀኙን ቋጠሮ
በግራው አዙሮ፤
ጥርሴን ከደንኩና … ሳቄን አቋርጬ
ውንድማችሁ እኔ
መሬት መሬት ማየት … አይኖቼን ሰብሬ።
በስንት መከራ … ህዝቡን አጩዋጩሆ
በሙግት ሳይቻል … በልመና ከፍሎ
ጨላዎቹን ይዞ … መልሱን ከኣንድ ብሩ
ከፊት ወንበር ያዘ … ከወዲህ ከወደ ዳሩ፤
ከሗላው ነኝና … የእኔም ተራ ደርሳ
ትኬቴን በስታልኝ … በብረት መቀሷ
ከወንበር ለማረፍ … ወደፊት ሳዘግም
ባሱ እየበረረ … ሲጓዝ ሳለ በጣም፥
ወደ ቤቷ ይሁን … ወይ ከሰፈር አምልጣ
ጥቁር ውሻ ዘላ … ከአስፋልቱ ብትገባ
ባሱን ቀጥ! አረገዉ … አይ ሹፌር አንበሳ
ደፍጥጧት ተጉዞ … እንዳይወጣ ነፍሷ፤
እኔ ግን ፈረዶብኝ … ተጣሞብኝ ገዴ
መቆም ስላልቻልኩኝ … ሚዛኔን አጥቼ
ስንደረደር ሄጄ … ከፊቴ ካለው ሰው
የዛን የባላገር … ማጅራቱን ብይዘው
አፍጢሜን ላተርፈው፤
ተፈናጥሮ ቆሞ … ፎክሮ እያቅራራ
ጊዜ እንኳን ሳይሰጠኝ … አፍታ ለይቅርታ
አገጬን ቢያነዝረው … በኣንድ ቡጢ ዱላ
መቋቋምም የለ … ዝምምምም በዪ በርሬ
አንገቴ ከመሪው … ሹፌሩ ላይ እግሬ፤
ህዝቡ ተጩዋጩሆ … ባሱም ጥጉን ይዞ
ደጋግፈው ቢያቆሙኝ … የኣዳም ዘር ተራድቶ
ሁለት ጥርሴ የለም … መንጋጋዪም ዞሯል
ነጭ ሸሚዝ ሱፌም … በደሜ ቀልተዋል፤
ተሳፋሪም ሲጮህ … “ፖሊስ ይምጣ” እያለ
እሱም ሲንጎራደድ … ግዳይ እንደጣለ
ከጎኑ ቁጭ ያሉት … አሮጊት ተጨንቀው
አሁን ደግሞ እንዳይዞር … የእኔ ዕጣ ለእሳቸው
በስመ-አብ፥ ወ-ወልድ … ሶስት ጊዜ አማትበው፦
“እባክህን ወዳጄ … ምንህን ጎንትሎት ነው
ይህን መሳይ ሽጋ … በአየር ያበረርከው
ደግሞም ያለ ሙያው … ሹፌር ያስመስልከው
ምንድነው ጥፋቱ … ከመሪው ያቆራኘው?”
ብለው ቢጠይቁት … ገላምጦ ትቷቸው
በአበጡት አይኖቼ … ቢያየኝ እኔም ሳየው
አልረካም መሰለኝ … ጮሆ እና አቅራርቶ
መጣ ተንደርድሮ … ካልጨረስኩት ብሎ፤
ዘጠኝ ፡ ኣስር ሆነው … ሴት ወንዱ ተናብረው
ነፍሴን ታደጉልኝ … ከመሃል ተሽጠው
አንድዪ ረድቷቸው።
በስንት መከራ … ጭቅጭቅ እግዞይታ
ጣቢያ ደረስንና … ነገሩ ሲጣራ፦
ወንዱን ልጅ እንደ ወፍ … በአየር ላይ አብርሮ
መሪ ያስጨበጠኝ … ሹፌር አስመስሎ፦
ቡጢ እንደ አረቄ … ናላዪን አዙሮ
በቁም ያሳለምኝ … ባሱ ማርስ ሲገባ መንኮራኩር ሆኖ
ሰዉ የጋማ-ከብት … መስሎ እስከሚታየኝ
ከሰማይ እንዳረግሁ … እራሴን ያሳተኝ
“ሰደበኝ፣ ዘለፈኝ” … ብላኝ “ተናገረኝ“
የሔድኩኝ ልቀጣው … ካሼሪዋ ጠርታኝ
“ባሱ” መስዪው ነው … ሳልቀድመው የቀደመኝ
በቡጢ የናደኝ፤
አይ ጉራማይሌ ቋንቋ … ስንት ጣጣ አመጣ
እንደው በአልባሌ … ድዴ ጌጡን አጣ።
ይህ ግጥም የተጻፈው ለኣንደኛ ደረጃ ትምህርት የአማርኛ መልመጃ ፡ የቤት ስራ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ግጥሜ እንደመሆኑ ዛሬም ድረስ ለግጥምም ሆነ ለስድ ንባብ ጽሁፎቼ ይዘት እና ጥራት ዕድገት መመዘኛዪ (Standard Unit) ነው። ስንናገር እንግሊዝኛ መቀላቅል ስልጣኔ ለሚመስለን፡ ለእኔ እና ለወገኔ “ገዳፋችን” ለሌላው እንዳይተርፍ ትምህርት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ።