Post

ግንቦት 20 የማን ድል ነው?

ግንቦት 20 የማን ድል ነው?

By Admin

የሚያወራ ሰው ሳያወራ ሲከርም “አፉን ይበላዋል ” ይባላል፥ የሚፅፍስ ሰው ከመፃፍ ሲቆጠብ ጣቱን ይሆን የሚበላው? ለዛ ይመስለኛል – እኔም ሰሞኑን ጣቶቼን አሳከከኝና ባስታግሰው ብዬ “ግንቦት 20 የማን ድል ነው?” ስል ጠየኩ።

በመሰረቱ “ድል” ማለት ትርጉሙ “ማሸነፍ” ወይንም  “አሸናፊነት” ብቻ ነው ብዬ አላምንም፤ እንደዛም ተብሎ መወሰድ የለበትም ባይ ነኝ። “ድል” የሚለው ቃል “ማሸነፍ” ከሚለው ፍቺ ባሻገር ሌሎች በተደራቢነት የሚገልፃቸው ተሳቢ ዕውነታዎችም አሉትና። በእኔ እምነት “ድል” ከድርጊት ገላጭነቱ በተጨማሪ የሚያጓጓ ውስጣዊ በረከት አለው። “ማን ማንን አሸነፈ?” “ምን በምን ላይ በረታ?” የሚለውን ሀቅ በሚገባ መረዳትም ለ”ድል” ያለንን ትርጓሜና ግንዛቤ ሙሉ ያደርገዋል።

ለምሳሌ ፦ መልካም ስርዓት መጥፎ አገዛዝን ሲጥል፣ ሲያሸንፍ (በጐነት በክፋት ላይ ሲበረታ)፥ ከመሸናነፉ ዕውነታ ባሻገር የአሸናፊው ባህሪ (መልካምነቱ) “ድል” የሚለውን ተወዳጅ ቃል እንድንጠቀም ሙሉ ነፃነት ይሰጠናል። ምክንያቱም “መልካሙ” “መጥፎውን” በማሸነፉ፡  ከድሉ ማግስት ጀምሮ የሚገለፁ ወይንም የሚታዩ መልካም ባህርያት (በረከቶች) አሉና። ያኔ፥ በማሸነፍና በመሸነፉ ሂደት ውስጥ ያለው አካል ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ቅን አስተሳሰብ ያለው ፍጡር በሙሉ “ድል” የሚለውን ቃል ለመቀበልም ሆነ የአሸናፊውን ድል አድራጊነት ለማመን አይቸገርም። ያንንም አጋጣሚ፦ ታሪክ “ድል” ብሎ ቢዘግበው፣ ህዝብ “የድል ቀን መታሰቢያ” ብሎ ቢዘክረው ተቃውሞ የለኝም።

በአንፃሩ ግን፥ በየትኛውም ቦታና ወቅት “ክፉ” አገዛዝ “መልካም” ስርዓትን ቢጥል (ክፋት በበጎነት ላይ ቢሰለጥን)፥ የክፉውን አሸናፊነት “ድል”ብሎ ለመቀበል የሚያገናዝብ ብሩህ አእምሮ ላለው ሰው እጅግ ይከብዳል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ በታሪክ ምዕራፍ ሲሰፍርም ሆነ ሲዘከር፡ የክፉው “ድል” ተብሎ ሳይሆን የመልካሙ “ሽንፈት” በሚል ዓምድ ሥር መሆን አለበት። ምክንያቱም ከክፉው አሸናፊነት (ድል) በስተጀርባ ለሰው ልጆች የሚተርፍ መልካምነት የለምና “ድል” የሚለው ማዕረጋዊ ቃል አይገባውም ብዬ ስለማምን። ይህ እምነቴ ደግሞ፦ በመልካም ላይ ክፉ ሲበረታ ብቻ ሳይሆን በሁለት የክፋት ሀይሎች ትግል መካከል ለሚኖረው የየትኛውም ወገን አሸናፊነትም መከራከሪያዬ ነው። ለዛሬ ጽሁፌ መግቢያ ይህን ያህል ከተንደረደርኩ፥ ግንቦት 20 መከበር ያለበት “የህወሀት ድል” ተብሎ ነው ወይንስ “የደርግ ውድቀት”?  የሚለውን ለእናንተ ልተወውና እኔ ወደ ርዕሳዊው ጥያቄዬ ልመለስ። 

በእርግጥ ግንቦት 20 የድል ቀን ነው? ከሆነስ፦ ለማን ምን መልካምነት አምጥቶ? ለእነማን ምን በጐነት ውሎ? ዛሬ ህወሀት በዋናነት “የድሉ ባለቤቶች ” የሚላቸው ብሔር-ብሔረሰቦች በግንቦት 20 የድል መድብል ውስጥ በስጋ እንጂ በመንፈስ አሉ? ድሉን ተከትሎ ከመጣው በጐ ለውጥ ተካፋይ ሆነው – በስም ሳይሆን በመብት “አጋር ድርጅቶች ” የሆኑት እነማን ናቸው? የየትኛው ክልል ህዝቦች ናቸው – ፍላጎታቸው በሀይል ሳይሆን በድምፃቸው ተከብሮ፣ ፍርዳቸው በጠመንጃ አፍ ሳይሆን በህግ መፅሐፍ ተዳኝቶ፣ በሀገራቸው ተገቢውን የዜግነት ክብር አግኝተው የዚህ ድል ባለቤት የምናደርጋቸው? ግንቦት 20 ለማን ምን መልካምነትን አስከትሏልና “ድል” ብለን እንጥራው? እነማንስ ድልን ተከትሎ በሚዘንበው በረከት ርሰው – የግንቦት 20 ድል ባለቤቶች እንበላቸው?

መቼም መፃፍ ፀያፍ ሆኖ የሚወገዙት፣ የሚከሰሱትና የሚታሰሩት ጋዜጠኞች፡ የእነ ተመስገን ደሳለኝ ድል እንዳልሆነ መገመት አይከብድም። የእነ አንዱአለም አራጌ፣ የእነ እስክንድር ነጋ፣ የእነ አቶ በቀለ ገርባ፣ የእነ አብርሃ ደስታ ድል እንዳይሆን ይህ መንግስት ያስጠለላቸው የጣር ቤት ጣሪያ ምስክር ነው።

ፈርኦን እንደገዛው የአይሁድ ባሪያ ድንጋይ እየፈለጠ ለጥቂቶች ስልጣኔ መታሰቢያ የሚሆን የዘር ፒራሚድ ሲገነባ የሚውለው የተማሪው ድል ነው? በዓመት ኣስራ አንድ ሴንቲሜትር በሜትር (ኣስራ አንድ በመቶ) ይመዘዛል በሚባልበት የኢኮኖሚ ዕድገት ሰርቶ መብላት አቅቶት፡ ድንበር ሲሻገር የአይሲስ ካራ፣ የሜድትራንያን ውሃ የሚበላው የወጣቱ ትውልድ ድል ነው? ወይንስ፦ የሀገራቸው ንብረት በሆነው አውሮፕላን በውጭ ቅጥረኞች እየተስተናገዱ ለስቃይና እንግልት በገፍ የሚኮበልሉት የሴት እህቶቻችን ድል ነው? ያለ ጧሪ ቀባሪ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ በፖሊስ ቆመጥ አባብጠው በየመንገዱ የሚወረወሩት፥ የወላድ መካን የሆኑት አዛውንቶች ድል ነው? ታዲያ ግንቦት 20 “የህዝብ ድል ነው” ከተባለ፥ የዚህ ድል ባለቤት የሆነው ህዝብ ማነው? የት አለ?

ህወሀት “የእምነት ነፃነቱን አስከብሬለታለሁ” የሚለው፡ የህዝበ ሙስሊሙ ድል እንዳይሆን፥ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ያለው እስር ቤት እንጂ ምክር ቤት አይደለም። ረመዳን ሄዶ ረመዳን በመጣ ቁጥር፥ መንግስት ይህን ማህበረሰብ በጥይት በስቶ በገዛ ደሙ ሲያስገድፈው እንጂ፡ ሃላዋ ጠቅልሎ በሳንቡሳ ቴምር ሲያስፈጥረው አላየንም። ክርስቲያኑንም ቢሆን እንዲሁ። የስጋ ጥላ ጎጆውን ብቻ ሳይሆን የነፍሱንም ታዛ ገዳማቱን ግሬደር ሲያርሰው፣ ባለሃብት ሲወርሰው፤ ዲያብሎስን በጾም ፀሎት የሚያስሩ መምህራን – በዲያብሎስ ሰንሰለት ሲታሰሩ ነው የምናየው።

ህወሀትን ከኣንድ ከህዋስ (cell) አንስተን፡ አባዝተንና አካፍለን እግር፣ ራስ እንዲኖረው ያደረግነው እኛ ነን የሚሉን መስራቾች “የተነሳንለት ዓላማ ይሄ አልነበረም ፤ ድሉን ተነጥቀናል” ብለው ካኮረፉ፤ አፋር፣ ጐንደር፣ ትግራይ፣ ሶዶ፣ ወለጋ፣ ጋምቤላ፣ ወዘተ … የሁሉም እንባ ካልታበሰ፣  የሁሉም ህመም ካልታገሰ – ታዲያ ግንቦት 20 የማን “ድል” ነው ብለን እንቀበለው?

አንተ ሰው – እንደ ሀይሌ ገብረስላሴ እግርህ ሲደክም ምላስህ መሮጥ ጀመረ? እንዳትሉኝ እንጂ፦ ግንቦት 20 የጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ የአቶ አባዱላ ገመዳም፣ የአቶ ደመቀ መኮንንም ድል አይደለም። መላ ደቡብ ሰላም አጥቶ ሲሰቃይ፥ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ቀበቷቸውን ፈተው “ሰለሜን” ከጨፈሩ፤ ለአረር አይደለም ለአርጩሜ እንኳን ገና አጥንት-ስጋዋ ያልጠነከረ የስምንት ዓመት ህፃን በጥይት ተደብድባ፥ አቶ አባ ዱላ ገመዳአኑ ሲያዳ” ብለው ከአቀነቀኑ፤ ጐንደር በሱዳን ጦር፣ ወልቃይት በህወሀት ጥይት ሲታደን እየተመለከቱ፥ አቶ ደመቀ መኮንን – የግንቦት 20 ድል የእኔ ነው ብለው ልፎክር ልሸልል ካሉ … መቼስ ምን ይባላል “ሆድ ይፍጀው ” ሳይሆን “ቀን ይፍጀው” ብሎ ማለፍ ነው።

በነገራችን ላይ፥ ድል ሲከበር እንደሚፎከር፣ እንደሚሸለል አሁን ነው ትዝ ያለኝ። ግን ምን ያደርጋል ዘንድሮ ድሉም ባለ-ድሎቹም ለፉከራ አይመቹም። ድሮ እንኳን ቢሆን፦ ኧረ ጐራው … ኧረ ጐራው … እንኳን እናቱ የወለድችውአማቱ ኮራች የተጋባችው፤ ዘራፍ … ዘራፍ … አካኪ ዘራፍ … ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻመድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤ ይባል ነበር። ዘንድሮ ጐራው ቀርቶ ጐሳው፣ ዘራፍ ቀርቶ ዝረፍ፣ በለው ሳይሆን ብላው፣ ጀግኖቹ መጡ ሳይሆን ጅቦቹ ወጡ ሆኗል እውነቱ። እስቲ ያም ቢሆን እንፎክር ካላችሁ ግን እሺ እንሞክር፦ ኧረ ጎሳው … ኧረ ጎሳው … እንኳን  ሚስቲቱ የዘረፈችውልጅቱ ኮራች የወረሰችው፤ ብላው … ብላው … የጣልያን አሽከር የኣረብ ደንገጡርየተራበው ጅብ ሲወጣ ከዱርእንኳን ብር ወርቁ የሚያዝሉት በእቅፍፎቅ ይሰወራል ይበራል በክንፍ፤ ዝረፍ … ዝረፍ … አንቃረህ ዝረፍ … ታምራት ቢሄድ ተተካ ጽዮንካዝና አገላባጭ ሰባ ቢሊዮን፤ ይብቃኝ መሰለኝ – ፉከራና ፉገራ ብዙም አይመቸኝም። ደግሞም የሰዎቹ እና የስኳር ምትሀታዊ ፍቅር ጅማሬው ገና ከጠዋቱ ሜዳ፣ በረሃ ሳሉ ነው። ዛሬ ከተማ ገብተው፣ በግላጭ ተገናኝተው ዶግ-አመድ ቢያደርጉት ምን ያስገርማል? እንኳን ለእንጨቱ ለአገዳው ማሳለአጥንት ለስጋ ለነፍስ አይሳሳ ብሎ መፎከር እንጂ።

ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነገር ልበል፦ ግንቦት 20 የእኔና የንስር ክንፍ ህብረት ድል አይደለም! ለዚህም ነው በዕለቱ ድህረ ገፃችንን  አጥቁረን የምንውለው። በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላሉ እኛን መሰሎችም የምናስተላለፈው መልዕክት ይህንኑ ነው። ቢቻል ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ጥቁር ልብስ በመልበስ፣ አመቺ ሆኖ ሲገኝም የግንቦት 20 ድል መታሰቢያ ፖስተሮችና ማስታወቂያዎች በተሰቀሉበትና በተንጠሉበት ምሰሶዎች ላይ ጥቁር ሪበን (ጨርቅ) በማሰር፡ ድሉ የጥቂቶችና ለጥቂቶች እንጂ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ በተቃውሞ ማሳየቱ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።

Comments are closed.