Post

ግን ለምንድን ነው?

ግን ለምንድን ነው?

By Admin

ልምድ ነውና ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ይህንኑ ድህረ ገፅ ገረፍ ገረፍ ማድረግ ጀመርኩ። ዓይኔ ውስጥ የገቡትን ብቻ ሳይሆን፡ ቀልቤንም ጭምር የሳቡትን አርዕስቶች እየፈተሽኩ አእምሮዪን በወቅቱ መረጃ ሳሟሽ፡ አንድ የአማርኛ ጽሁፍ አነበብኩና ንድድ አልኩ።

ግን ለምንድን ነው፦ እኛ እኛን ሆነን መስሎ ማደርን ማቆም የተሳነን? ግን ለምንድን ነው፦ ዕውነትን አምጠን፣ ወልደን፤ ከዕውነት ጋር አድገን፣ አርጅተን፤ እውነተኞች ሆነን ከዕውነት ጋር መሞት ያቃተን? ስል ጠየኩ። በቃ አለ አይደል … ማን ምንም ይሁን ምን … ብቻ እኛ እኛ እራሳችንን የምንሆነው? ክሳችን፣ ምስክርነታችን፣ ፍርዳችን በወቅት ላይ ሳይሆን በሃቅ ላይ ብቻ የሚደገፈው?

ቀድሞ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዴምህት) ሊቀመንበር፡ በኋላም የአገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ ምክትል የነበሩትን ግለሰብ “መኮብለል” አስመልክቶ ብዙ ተብሏል፤ ብዙም እየተባለ ነው። ዛሬ በዛ ላይ የምደምረው ሃሳብ ባይኖረኝም፥ እውነታው ግን ከእልፍ-አእላፍቱ ክዋክብት መካከል ኣንዱ ቢወድቅ ቢነሳ፣ ቢደምቅ ቢደበዝዝ፣ ቢጠፋ ቢበራ የምሽቱን ሰማይ ውበትና ግርማ ሞገስ አይገፈውም። የአቶ ሞላ አስገዶም ከትግሉ ጎራ “መነጠልም” ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይሆንም። ይህንን ስል፥ ጉዳቱ ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታዊ ተፅዕኖ አይኖረውም ለማለት ፈልጌ እንጂ፤ በጭፍን ተነስቼ በትግሉ ላይ የሚጥለው ምንም አይነት የሞራልም ሆነ የስነ-አእምሮ አሉታዊ ጥላ የለም በዪ ለመካድ አይደለም። ይህ ሆነ ተብሎ ግን ትግል አይቆምም። ዛሬ በየአደባባዩ የምንመለከተው እምቢተኝነት ብሶት የወለደው፣ ተስፋ መቁረጥ ያማጠው እንጂ ከትግሉ ጎራ ሞልቶ የፈሰሰ ጀግንነት አይደለም። እንኳን ገና በዝግጅት ላይ እያለ ቀርቶ፡ ከተፋፋመው የፍልሚያ አውድማ መሐል ገብቶም ድንገት ሳይታሰብ የሚያመልጥ አለቃና ጀሌ ነበር፣ አለ፣ ደግሞም ይኖራል።

ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ ግን የአቶ ሞላ አስገዶም “መክዳት” ሳይሆን ወሬውን ተከትሎ የማነባቸው መጣጥፎች፤ በተለይም የግለሰቡን ባህሪ አስመልክቶ፦ አግኝተነው አናዘነው ነበርየበረሃውን ንዳድ በመሎቲ ቢራ አብረን አብርደናል ከሚሉት ግለሰቦች የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ናቸው። ጎበዝ እስቲ ትንሽ እንኳን ሰብዓዊ ግብረ-ገብ ይኑረን። ዛሬ የሚሰማን ጆሮ እኮ ትላንት ያዳመጠን ነው፤ ነገም ስንናገር እንዲሁ። እንኳን ምላስ፡ ጃኬትም ተገልብጦ ሲለበስ ለዓይን ይቀፋል። ያውም በዚህ ፍጥነት። ትላንት በቀጠሮው ሰዓት ከተፍ ያለ – አብሮንም ቁርስ የበላ አንበሳ ነው ያሉትን ፤ ዛሬማልዶ እብስ ያለ – አፈር የበላ ውሻ ነበር ብሎ መራገም ያሳዝናል። 

ከማሳዘን አልፎ የሚያሳፍረው ደግሞ፦ የግለሰቡን ዕምነት አጉዳይነት እናውቅ ነበርያልተናገርነው ትግሉን ይጎዳል ብለን ነው ሲባል ነው። ዛሬስ ትግሉን ጠቀመ? እንደ እኔ ዕምነት ከሸሹት ከአቶ ሞላ አስገዶም ይልቅ ትግሉን የሚጎዱት፦ መሃላችን ያሉት አቋም የሌላቸው፣ የአንገታቸውን ክር በጥሰው አንጀታቸውን እንደ ማተብ ያሰሩ፣ ሆዳቸው ሀይማኖታቸው የሆነ፣ ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት ግለሰቦች ናቸው። ለእኔ በምድሩም ሆነ በሰማዩ ክብር የማይገባቸው፦ የእግራቸውን ጫማ እንደ አቦሸማኔ ቅልጥም አርዘመው – ፈርጥጠው ከአይን የሚሰወሩት ከሃዲዎች ሳይሆኑ፤ የእጃቸውን ማይክራፎን እንደ ወባ ትንኝ ፕሮቦስስ (proboscis) የተገኘው አካል ላይ ሰክተው – ተክለው፡ ዛሬ ሌላ ነገ ሌላ እያወሩ ደምና ብር የሚመጡት አስመሳዮች ናቸው። ነብዩ ኤርምያስም የነገረን ይህንኑ ነው፦ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ: ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች” (ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 11)

ትዝብት እና ንዴት ቅደም-ተከተሉን አስረስተውኝ ይህን ያህል ቢያስጉዙኝም፡ ከከፋ ወቀሳ ለመዳን መጀመሪያ መሆን የሚገባውን መደምደሚያ አድርጌ፡ የኢትዮዽያውያኑን ዘመን መለወጫ ለምናከብር ሁሉ መልካም አዲስ አመት ይሁንልን! ማለት እወዳለሁ።

ትግል ጠላትን ጥላሸት በመቀባት፣ በማቆሸሽ ብቻ ሳይሆን የራስንም ጉድፍ በማጠብ፣ በማፅዳት፣ ራስን ሆኖ በመቆምም ይገለፃል!

Comments are closed.