
By Admin
ሳይደግስ አይጣላም ነው ተረቱ ፣ እንደው የአንድ ለሊት እድሜ ብቻ በመያዛቸው ነገሩ አማረ እንጂ ፥ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባችን ውሰጥ በየቤቱ የሚደገሱት ልበል የሚጠሩት ፓርቲዎች የነወጠመቬን ጉልበት በቁማቸው ባሰለሰሉት ነበር። ታዲያ ምን ዋጋ አለው እድሜያቸው ቢያጥርም ውለደታቸው በዛና ግን አለሸሹም ዞር አሉ ሆነ ነገሩ።
ትላንት ኪኪ ቤት ከባህር እንደሰጠመ ጀማሪ ዋናተኛ ነፈሱን በባዶ አየር ሲቀዘፍና ሲያዝቀዝፍ የነበረው ጆሲ፥ ዛሬ ደግሞ ከነ ጢጢ ቤት ለተመሳሳይ ትዕይንት ፕሮግራም በመያዝ ጉልበቱን በማይረባ ጨረባ ያዳከማል እና ተረቱን ጠቀሰኩ። ጎበዝ፥ ምነው ግን እነዚህ በእኩለ ለሊት ተነስተው በአበደ የፈረንጅ ሙዚቃ ምድር ሲደበደቡ ጎረቤት አላሰተኛ የሚሉትን ፓርቲኞች “ሃይ!” የሚል ጠፋ? ዜጋ በፅልመት የባህልን ድንበር ሲጥስ ፣ ዜጋ በውደቀት በአልባሌ ጮቤ የጉልበቱ መቅኔ ሲፈስ ፣ መንደር ጎረቤት እረፍት ሲያጣ እንዴት ዝም ይባላል?
ይብላኝ አርጅቶ ጉልበት ላጣው እንጂ እኔማ ምንተዳዬ ፤ በአጎራባቾቼ የፓሪ ሙዚቃ ጩኸት እና በአስረሽ ምቺያቸው ሃሴት አድርጋ ከምትርገፈገፈው የኪራይ ቤቴ ጋር ሆኜ ፤ አንዴ በግራ አንዴ በቀኝ ጎኔ እየተገላበጥኩ አስነካዋለሁ። ጉዱ ግን እንደ አከራዩኝ አሮጊት ያረጀቸው የጭቃ ቤቴ ግድግዳ በቢቱ ውዝዋዜ እርግብግቢቷ በዝቶ አቅም አንሷት ከላዬ ላይ ዘፍፍፍፍፍፍ! ያለች ቀን ነው።
ወገን፥ እኔኮ የሚገርመኝ ይኼ ከጉለሌና ከገርጅ፥ ካሳንችስ ቦሌ ተሰባስቦ ሲሞዝቅ እና ሲያሟዝቅ የሚያነጋው ሁሉ የት ገባህ፣ የት ወጣህ፣ የት አመሸህ፣ የት አደርክ እያለ የሚቆጣጠር ወላጅም የለው እንዴ?
ግን ምን … ዛሬ ዛሬማ የመኪና መንገድ እንኳን ብቻዋን እንድትሻገር ለመልቀቅ ከምታሳቅቅ ሚጢጢ እንስት ጋር እጅ ለእጅ ተቋልፎ ወደ ፓሪ ተብዬው ቤት የሚነዳውን ተባዕት ለተመለከተው፥ የተጣሉ ባልና ሚስት ሊሸመግል እንጂ እውን ወደ አስረሽው-ምቺው ቤት ነው የሚክለፈለፈው ብሎ ለማለት ፈራጅን ይፈታተናል። ታዲያ ወላጅ እንዲህ ሲቀል ተወላጅ ምን ያድርግ?
እንደው የዚህ የፓሪ ነገር ሲነሳ ሁሌ ትዝ የሚሉኝ የአንድ ጓደኛዬ አያት ናቸው። እስቲ እግረ-መንገዴን እንዴት አመሸሽ ልበላት ብዬ ጎራ ካልኩበት ቤት “ቁጭ በል” እንኳን ያላለችኝ አብሮ አደጌ እንደቋንቋቸው “ዛሬ ባክህ ልወጣ ነው” ብላኝ ፥ ከመስታወቱ ፊት ለፊት ቆማ አንድም የአሜሪካን የስፖርት አይነትና የከተማ ስም ያልቀረበትን ቀሚስ አይሉት ቲ-ሸርት አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደታች እየጎታተተች መከራዋን ስትበላ ያዩዋት አያት ፥ በእሷ ሁኔታ ይሁን በልብሱ የተገረሙበትን ሁኔታ ባላውቅም ፥ የዕድሜ መርፌ የዘመዘመውን ፊታቸውን ይበልጥ ሸብሸበው “ኤዲያ! ጩኒ እንደውኮ ዝም ብለሽ ነው እንጂ ይህንንስ ከምታጠልቂ ለሚያይሽም ጡሁፉ የሚገባውን የእኛኑ የሀገራችንን ጋዜጣ ለብሰሽ በወጣሽ ይሻል ነበር” ያሉት እስከመቼውም ከአእምሮዬ የሚጠፋ አይደለም። እውነትም ጋዜጣ … .
ልብ ላላቸውማ ከፓሪቲው ብዛት ይልቅ የፓርቲኞቹ ነገር ያስገርማል። ጊዜ ኖሮት ለማድነቅም ባይሆን ለማዘን ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍራቸው ለተመለከታቸው እንደው ትንግርት ናችው። የጠርሙስ ስባሪና የበሬ ቀንድ ሊደረደርበት ትንሽ ወራት ከቀረው ፀጉራቸው ላይ የሚታየው የዶሮና የአሞራ ላባ፣ ክብደት በዝቶበት ተገንጥሎ ሊወድቅ አንድ ሐሙስ የቀረው ከሚመስለው ጆሮዋችው ላይ እንደ ግንበኛ ቱንቢ ረዝሞ የተንጠለጠለው የብስክሌት ቸርኬ የሚያክል የጆሮ ጌጥ፣ ከአንገታቸው የሚያጠልቁት የጎልማሳ አንበሳ ማሰሪያ እንጂ ማጌጫ ከማይመስለው ሰንሰለት … ኸረ ምኑ ቅጡ፥ በአጠቃላይ ከእነ ምናምንቴያቸው ጋር የጋራዥ መፍቻ ሳጥን መስለው ችለው እና ጉልበት ኖሯቸው ሲራመዱ ላያቸው ታሪክ ናቸው፤ አሳዛኝ ታሪክ።
እስቲ እኔም አስራ-ሁለተኛ ክፍል የነገር አለሙ ማብቂያ ሆኖ “ማትሪክ ወሰድኩ” ብላ አንድ ተማሪ ካዘጋጀችው የጭፈራ (የፓሪ) ትዕይንት ላይ ተጋባዥ ሆኜ የታዘብኩትን ልንገራችሁ። ታዲያ ነገሩ አንድም በዝምድና ሁለትም በድንገት የተከሰተ ነውና “ጅራፍ እሱው ገርፎ …” እንዳይባልብኝ አደራ።
ይገርማል፥ ከሰላሳ-አምስት ከማናንሰው ወንድ እና ሴት ወጣት ሁሉ በዚያን ቀን በዛ ቦታ አምስት ፊደል ያለው መጠሪያ ስም ይዘን የተገኘን እኔና የቤቱ ዘበኛ “ደምሳቸው” ብቻ ነበርን ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ፓርቲው ተጀምሮ እስኪያልቅ የሰማሁት ስም ሁሉ፥ እነሱው ይሁኑ ወላጅ ምንጩን ባላውቀውም ሁሉም የያዙት መጠሪያ የሁለት ፊደል ጥምር ነበር። ሴቶቹ እንደ ፈረንጅ ቡችላ ዶኒ፣ ሲቲ፣ ኩቲ … ሲባባሉ፤ ወንዶቹ በተራቸው ደግሞ ጭሱ፣ ጉሙ፣ ፍሙ … እየተባባሉ ሲጠራሩ ያየና የሰማ እማኜ ይሆናል። ምን ይሄ ብቻ እናቶቹም ማሚ ፣ አባቶቹም ዳዲ ሆነዋል እንጂ። ሌላ ሌላውማ አይነሳ … .
እንደኔ እንደኔ የመግባቢያ ቋንቋውንስ ነገር እዚያው በጠበሉ ብሎ ማለፉ ብቻ የሚሻል ነው የሚመስለኝ። አለበለዚያ ግን ወደ ፓሪ ቤታቸው መሔድ ማለት ወደ ሌላ ዓለም መግባት ሆኖ ቱርጅማን እንደሚያስፈልግ ያወኩት፥ እንደ ስጦታ ዕቃ መጠቅለያ ወረቀት ከተብለጨለጩት እንስቶች መካከል ዕጣዬ ሆና “ታጫውትህ” ተብዬ የተሰጠችኝ ሊሊ መሃል ለሊት ላይ “I wanna coffee” ብትለኝ፥ ከላይ ታች ተንከራትቼ፣ የቤት ሰራተኛ ተማፅኜ ስጣደፍ ያመጣሁላትን ቡና ለጓደኞቿ እያሳየች ገልፍጣ ስታስገለፍጥብኝ ነበር። ታዲያ እኔ “ፋራው” ምን አባቴ አውቄ፥ ለካስ ስሰማ ምሁሩ የፓሪው ቤት ተርጎሚና ደራሲው አይታወቅ እንጂ፥ በፓሪው ቤት የመዝገበ ቃላት ፍቺ መሰረት I wanna coffee ማለት “ቡና እፈልጋለሁ” ሳይሆን “መሳም እፈልጋለሁ” ኖሯል። አይ ፈጣሪ አሉ አያቴ፦ እሳት ይሳማትና።
እንደው ለጊዜውም ቢሆን ሁኔታው አሳፍሮኝ አንገቴን ቢያስቀረቅረኝም፥ ዲጄው ሲሞዝቅ ግን ፊቱን ወደ ሰማይ አንጋጦ፣ ጉልበቱን እያሸባረከ ውሃ ከጉድጓድ በመዘውር ይስብ ይመስል የግራ ቀኝ እጁን እያፈራረቀ ከኮርኒሱ ጥግ እያደረሰ የሚመለሰውን “ፍሪክ” “ምን ሊጨብጥ ነው?” ብዬ ቀና ብል ፣ ያ እግዜር ያልሰጠውን መጋጠሚያ ለአካሉ አበጅቶ ሲቀነጣጠስ በፉጨትና በጭብጨባ አድናቆት የሚቸረውን “ብሬክ” ዳንሰኛ አይቼላችሁ፥ ሰይጣን ይሁን ስልጣኔ ምን እንደገፋፋኝ ሳላውቀው እሱን ልምሰል ብዬ አንዴ አንገቴን ባዞረው፥ ጅማቴ ተጠማዞ አገጬ ከትከሻዬ ላይ አረፈና እንዴት ከቦታው ይመለስ? የአርባ-አራቱን ታቦትና ገዳማት ስም እስከነ ቀናቸው እየጠራሁ ዣንጥላ ፣ ጧፍ ተስዬ፥ አገጬን በሁለቱ እጆቼ እርዳታ ከመደበኛ ቦታው መልሼ ከዛ የተረገመ ቪላ አቀርቅሬ ወደ ቤቴ ብሾልክም አንድ ስጋት ግን በልቤ ይዤ መውጣቴ አልቀረም።
ዛሬ … ዛሬ በየቦታው ውሻዬ ቡችላ ወለደች፣ አውራው በግ ታረደ፣ የዶጮ ድብርት፣ የድመቴ ስንብት እያሉ ከተማውን ሰዶምና ጎሞራ አስመስለው ጮቤ የሚረግጡት እነ ኒኒ፥ ነገ … ነገ ደግሞ የዳዲ ሙት ዓመት ፣ የማሚ ሰማንያ እያሉ በማይሆን ውዝዋዜ የዜጋውን ጅማት አጠላልፈው እንደ አከርካሪው ሁሉ ሞራሉንም እንዳያሽመደምዱት ጭንቀቴ ሆኗል። ምናለ መንግስትስ እንደ “ቅሌታሞቹ” መፅሔትና ቪዲዮ ቤቶች ሁሉ እነዚህ በየመንድሩ የሚጠሩትንም ፓርቲዎች አንድ ቢለን?
1984 ዓ.ም.