Post

ጨረቃው መንግስታችን

ጨረቃው መንግስታችን

By Admin

አነሳሴ ፀሐዩ መንግስታችንበመባል የሚታወቀውን የቀድሞውን የቀዳማዊ ኃይለስላሴን አገዛዝ ከዘንድሮው ንጉሣዊመሰል ሥርዓት ጋር ለማወዳደር አይደለም። የእኔ ጨረቃ በተለምዶ የጨረቃ ቤት” “የጨረቃ ምርጫወዘተ እየተባለ እንደሚጠራው ህገወጥነትንየሚጠቁም ለዛም የላተም። የዚህ ጽሑፌ ጨረቃትርጓሜ ልማደወጥ እውነታን ለማሳየት ሳይሆን ባሕሪአልባ ገፅታን ለማጉላት ነው።

ድቅድቅ ባለው ጨለማ ውስጥ ድንገት ፍንትው የምትለው ጨረቃ እንደ ድሮ ልጃገረድ ገፅታ ቀልብን ትገዛለች፤ ኧረ ኣንዳንዴም ልብን ትስርቃለች። እውነታው ግን አማላይዋ ጨረቃ … ዕድሜ ለፀሐይ!ትበል እንጂ … በውስጡዋም ይሁን በላይዋ የእኔ ነው የምትለው ቅንጣት (0.0001 lumens ) ብርሃን የላትም። ታዲያ ያ ማራኪ ውበት፣ ብሩህ ብርሃን ከየት መጣ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የgoogle search box አለና … እኔ ወደ ጨረቃው መንግስታችን ልመለስ።

ብልፅግና ልክ እንደ ጨረቃ … መንግስት ያልሆነ ነገር ግን መንግስታት ነን ከሚሉ ሀገራት የመንግስትን ስነባህሪ ተቀብሎ መልሶ በማንፀበረቅ መንግስት ለመምሰል የሚሞክር የግብዞች ስብስብ ብቻ ሳይሆን፤ ልክ እንደ amoeba (አሜባ) የእራሱ የሆነ ቅርፅና መጠን ኣልባ አካልም ጭምር ነው። ከዚህም የተነሳ ነብዩ ኤልያስ ወደ ምድር ቢመለስ እንኳ … የነገን የብልፅግና አቋም መተንበይ ቀርቶ ዛሬ ላይ ያለውን ባህሪም ቢሆን በቅጡ መናገር የሚችል አይመስለኝም። ከኣፍ እስከ ገደፉ አማኞች ነንበሚሉ እምነትናቂ ዘረኞች ለተሞላው መስተዳድር … “ኣንድ ሺህ ዘመን እንደ ኣንድ ቀን፥ ኣንድ ቀንም እንደ ኣንድ ሺህ ዘመንነው። በየሰከንዱ ለመቀያየር ከበቂ በላይ ጊዜ አለው።

ብልፅግና ከውጭ ወደ ውስጥ ለምንመለከተው ባይተዋር ዜጎች ብቻ ሳይሆን፥ ከውስጥ ወደ ውጭ ለሚያዩት ቤተኛ አባላቱም ቢሆን እንዲሁ ወጥአልባ (abstract) ድርጅት ነው። ለዛም ነው ኣንዱ ባለስልጣን tweeter ላይ የነገረንን … በዛው ቅፅበት ሌላው telegram ላይ ወጥቶ የሚሽረው። ፓርቲው እንኳን ለሚመራቸው ዜጎች … ለሚመሩትም ዘገምተኞች ቢሆን የጋር መግባቢያ ሆኖ የሚያገለግል ምስልም ሆነ ባህሪ የለውም።

ዛሬ ላይ እንደምናየው ኣፋር ተወረረ ኣማራ ተለቀቀ፣ ኣማራ ተለቀቀ ኣፋር ተወረረ … እያልን እንዲህ በፈረቃ የማበዳችን ሚስጥርም ይህንን የብልፅግናን ጨረቃዊ ባህሪ ካለመረዳት የመጣ ችግር ነው። ይህ ብቻም ደግሞ አይደለም ሀገር ዕውቀት ስልጣን በሰጣቸው ምሁራን ሳይሆን፥ ስልጣን ኣዋቂ ባስመሰላቸው መኃይማን ስትመራ የምትጓዘው እንዲህ በሦስት ማዕዘን ጎማ ነው። እየተነሱ መውደቅ፣ ከፍ እያሉ ዝቅ ማለት የየሰከንዱ አደጋ ይሆናል፤ መንገጫገጩ ይበዛል።

እርግጥ ነው መፅሐፉም ቢሆን ጥበብን (ዕውቀትን) ገንዘብህ አድርጋትይላል፤ እየመነዘርክ እንድትጠቀማት ብቻ ሳይሆን ሌላውንም እንድትጠቅምባት። የጥበብ ገንዘብን የመሆን ምሳሌ ግን ማንም ያለ ሥራ ቀብድ እንዲወስዳት አያደርጋትም። በዚህ በጨረቃው የብልፅግና መንግስት የምናየው እውነታ ግን ይኼንኑ ነው። በየሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ከእምነቱ ቡራኬ እስከ ፖለቲካዊው ትንታኔ በሚዘጋጁት ህዝባዊ መድረኮች ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት እንደ ጨረቃዋ የራሳቸው ብርሃን (ዕውቀት) የሌላቸው ነገር ግን ብሩህ መስለው ለመታየት የሚሞክሩ ግብዞች ናቸው። ዲግሪ ዲፕሎማና ሥልጣን በቀብድ የተቀበሉ ዘረኛ እብዶች።

ከእነዚህ በላይ የሚገርሙት ደግሞ፦ ነጮቹ እንደሚሉት የተቀደደ ጫማ አድርገው ታዋቂ ጫማ ሰፊዎች ነንበማለት እግር ይዘው አላራምድ የሚሉት ብልፁግ “የማህበረሰብ አንቂዎቹ” ናቸው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በድንገት የሰማሁት ኣንድ ድምፃዊ ይህን መሳይ እውነት በዘፈን ስንኝ ሲገልፀው እንዲህ ነበር ያለው፦

የዘንድሮ ዐዋቂ ጨዋ በኣደባባይ

ፀሐይ ልሁን ይላል የጨለመበት ሲያይ

ገራሚ ትዝብት! ኣራት ፍሬ ቤተሰባቸውን በትነው መቶ ሚልዮን ህዝብ በኣንድ ጣሪያ ስር ለማኖር የሥነልቦና ምክር ካልሰጠን ብለው ከግሩቭ ጋርደን የሚያጓጉሩት የብልፅግና ካድሬዎች ይህን ግሩም ዘፈን ሰምተው ይሆን?

አጭር ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት ግን፥ የዚህን መንግሥት ጨረቃዊ ስሪት ለተረዳ አእምሮ እንዲህ በየሰዓቱ ብልጭ ድርግም ማለቱ አረማመዱን ከእንቅፋት ብቻ ሳይሆን እምነቱንም ከተስፋ መቁረጥ እንደሚታደገው ማስገንዘብ እወዳለሁ። መንግሥት ያልሆነውን መንግሥት መሳይ፦ ኣፋርን ከህወሃት ኣማራን ከኦህዴድ ተከላከል እያለ ነጋ ጠባ እሰጣገባ ውስጥ ከመግባት ይታደጋል። መሆን ያለበትን በጊዜ መክሮ ከዚህም በላይ እጅግ ሳይረፍድ ወደ ተግባር ለመግባት ያነቃል። ይሰማል? ደግሞስ መንግስት ከተግባሩ መች ቦዘነ? ከተናገረውስ ምን አጎደለ? እንኳን ቃሉን ትንቢቱንም በትጋት ፈፅሟል፥ ነገም ይፈፅማል። ለዚህም መከራከሪያዬ ብዙ ነው። ትዝ ይላችኋል? በኣንድ ወቅት ጨረቃው ጠቅላይ ሚንስትር ግዴለም ትንሽ ታገሱ እንጂ እጃችሁን በኣፋችሁ ላይ አስጭናችኋለሁብለው ሊያስገርሙን ትንቢት እንደተናገሩልን? የእናንተን ባላውቅም እኔን ግን በግርምትም ባይሆን በሀፍረት እጄን በኣፌ ላይ ካስጫኑኝ ሰነባብተዋል። ይኼ ብቻም አይደለም፦ ድላችን ሰበር ዜና አይሆንምብለውንም ነበር እኮ። ታዲያ መቼ ዋሹ? ከኣፋር እስከ ኣማራ በሴራ ረግፈው፣ ከህፃን እስከ መንኮሴ በስድ ተደፍረው፣ ህዝቡ ከቅልጥም እስከ ቅስሙ ተሰባብሮ እንክትክቱ ከወጣ ቦኃላ ህወሃት ጠፋቢባል እንኳ ሰበር ዜና የሚሆነው ለማን ነው? ለነገሩ መንግስት ህወሃትን ሊያጣፍጣት እንጂ ሊያጠፋት ፍላጐትና ዕቅድ ያለው አልመሰለኝም። ጄነራል ባጫ ደበሌ መቀሌን ቀስ እያልን ሹርባ እየሰራናት ነውሲሉን ሊደልሏት እንጂ ሊድሯት … እንዲህ በድርድር አስውበው ሊሞሽሯት እንዳሰቡ ማን ጠረጠረ?

የከርሞ ሰው ይበለን እንጂ በጨረቃው መንግስት ምን እውነት ምንስ እምነት አለ? እዛው መስቀል አደባባይ ላይ ክብርት ከንቲባዋ … ንግሥት ጉዲት ሁለተኛተበለው ሲቀቡ፣ ዳግማዊ ዮዲትሆነው ሲነግሱ እናይ ይሆናል። ገንዘብ ያጠረው መንግስትመሳይ መንግስት ግንባር ለግንባር እየዞረ ፥ ወታደራዊ ሹመትን በወርሃዊ ደሞዝ ፋንታ እንደ ብር እየቆጠረ መክፈል ከጀመረ … ያኔ … anything is possible!

Comments are closed.