
By Admin
ገና ከትምህርት ቤት እንደወጣሁ ነበር። በስራው ዓለም የመጀመሪያዬ ለነበረው ሴሚናር ወደ ሰሜን ከማቅናቴ በፊት ኣንድ አንድ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ከቢሮ ወጥቼ አዲስ በተቀጠርኩበት መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው ቤተ- መፃሕፍት ጐራ አልኩ። ይጠቅሙኛል ያልኳቸውን መፅሐፍቶች ከመደርደሪያው ላይ ለቃቅሜ ከመቀመጤ ፥ ስገባ በቤተ-መፅሐፍቱ ቀኝ ጠርዝ በሚገኘው፣ ዙሪያውን በመስታወት በታጠረው ሰፊ ቢሮዋ ውስጥ ተቀምጣ የአንገት ሰላምታ የተለዋወጥነው ወጣት librarian ወደ እኔ አቅጣጫ ስታመራ ተመለከትኩ። ደንብ ነውና ከመቀመጫዬ ተነስቼ ከተጨባበጥን ቦኋላ፥ “ግቢውን ለመድክ?” ስትል ጠየቀችኝ። ቀናት አልፈው ወደ ሳምንቱ ስለተጠጋሁ- “አዎን … በሚገባ ለምጃለሁ” ስል መለስኩ። ከጥቂት ጥያቄና መልሶች ቦኃላ፥ እኔም ከወንበሬ ላይ ተቀምጬ እሷም በሁለት መዳፏ ከእኔ ትይዩ የነበረውን ወንበር መደገፊያ ጠርዝ እንደዋዛ እየደባበሰች ፥ “ህይወትስ እንዴት ነው?” የሚለው ጥያቄዋ ተከተለ። እባብ ለእባብ … ይተያያል ካብ ለካብ እንደሚባለው፥ ጭንቀቱዋ ከኣዲሱ መስሪያ ቤቴ ጋር መላመዴን ማወቅ ሳይሆን እኔን ከ”እየሱስ ጋር ማስተዋወቅ” እንደነበር ወዲያው ገባኝ። አልተሳሳትኩም፤ “ጌታን ተቀብለሃል?” ፈገግ እያለች የጠየቀችኝ ቀጣይ ጥያቄዋ ነበር። ለጥቂት ሰከንዶች ተፈተንኩ። ከመቀበልም አልፌ እስከ እነሱ ሰፈር ድረስ የሸኘሁት እኔ እንደሆንኩ ነግሬ፥ ያንን እንደ እሳት ለሚለበልብ አፍላ የወጣትነት ስሜት እፎይታ የሚሰጥ ለስላሳ ድምፅ የምሰማበትን አጋጣሚ በአጭር መቁረጥ ነፍስ የመቅጨት ያህል መስሎ ዘገነነኝ፤ “አለተቀበልኩም” ብዬ ለመካድም የሲዖል እሳት ወላፈን ከሩቅ ገረፈኝ። ብቻ በደፈናው “ብዙ እንቆቅልሽ አለኝ” ብዬ “ለመማማር” ቀጣይ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን።
ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በመስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ አልነበርኩምና ቆይቶ፥ በኣንድ የእረፍት ሰዓት በመስሪያ ቤቱ ክበብ ከሌሎች ባለደረቦቻችን ጋር ከበን እንደተቀመጥን፥ እንቆቅልሼን ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ነገረችኝ። ቃል በቃል ለማስታወስ ብቸገርም፥ የጥያቄዬን ጭብጥ ግን አሁንም አልዘነጋሁትም። ስደት፣ ሞትና እምባ በድሆች አምባ ገነዋል፤ እዚህም እዚያም በሚለኮሰው ጦርነትና አምባጓሮ ምድር በመበለቶች እሮሮ ደንቁራለች፤ የምስኪኖች ጩኽት እንኳን የሰራቸውን፥ የሰማቸውንም ነፍስ ያዝላል፤ ታዲያ ይኽን ሁሉ ግፍና መከራ አይኑ እያየች እንዴት ዝም ይላል? የሰው ልጆች እንዲህ በስቃይ ለሚያሰሙት የማያባራ ሲቃስ ማነው ተጠያቂው? ስል ነበር የጠየኳት።
የዚህችን ክፉ አለም ክፋት ባየሁት ልክ ለማሳየት ብዙ ብቸገርም፥ ከዛች ፍልቅልቅ ወጣት አፍ በቁጣ ተፍለቅልቆ የወጣው ቃል ግን እንደወረደ ይኼ ነበረ፦ “ሰይጣን ነዋ! የክፋት ሁሉ ምንጭ የሆነው – ዲያብሎስ! እግዚአብሔር ይገስፀው!” … ስትል እሱን ሳይሆን እኔኑ እራሴን የገሰፀችኝ መስሎ እስኪሰማኝ ጮኸች ። ሆኖም፦ “አልተቀበልኩሽም” አልኩ። አሁን ግን ያ ለስላሳ ድምፅ አሳስቶኝ ክርክሩን ለማርዘም ሳይሆን በእርግጥም ስላልተስማማሁ ነበር ። መጽሐፉ እንዲህ ይላልና፦
አዎን … ከመከራው ፅናት የተነሳ ለጆሮ የሚዘገንን እሮሮ የሰማው የሰማርያ ንጉስ ልብሱን ቀዶ ሰይፉን የመዘዘው፣ ከቦ ላስጨነቀው ለሶርያው ንጉስ ራስ ሳይሆን፥ አብሮት በከተማው ውስጥ ለተከበበው፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለኤልሳዕ አንገት ነበር። ለምን? ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ። እስከ አሁን ከመጣሁበት በላይ ብዙ ሰለሚያርቀኝ። ባይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩን ጠይቋቸው። አሁን በቅርብ፦ ፈጣን በሆነ የማስመሰል ፈረስ እየጋለበ ውሎው ቀራንዮ አዳሩ ሰዶም ገሞራ የሆነውን “መሪ – ክርስቲያን” ሰብስበው፦ “እናንተ ጋር ቢኖር ኑሮ እኔም ጋር ትንሽ ይመጣ ነበር” ሲሉ ብሰማቸው፥ እንደገባኝ የገባቸው መስሎኝ ነበር። ግና ብዙም ሳይቆዩ፥ እራሳቸውን ከደሙ ንፁህ አድርገው “እግዚአብሔር ይፈረድባችሁ!” ብለው ሲራገሙ ሰማኋቸው። እንደ ሰማርያው፥ የሰማዩም ንጉስ ቁጣ ሲነድ፣ የወገቡ ሰይፍ ለፍርድ ስትመዘዝ ከቤቱ ደጃፍ እንደሚጀምር አያውቁ ይሆን?
ሌላው በጨረፍታ ልነካው የምፈልገው … በእምነትም ይሁን በጐሳ ጥምረት እውነትን ማጠልሸት ፈፅሞ እንደማይቻል ነው። ይኽን እንድል ያስገደደኝ የአቶ ጃዋር መሐመድ ከኤል ቲቪ ጋር ያደረጉት “ጥናታዊ” ቆይታ ነው። ኤል ቲቪ የማን ንብረት እንደሆነ የጠየቀ፣ የ”ጥናታዊ” ቃለምልልሱንም ዓላማ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ሲጠየቅ ከጋዜጠኛዋ አፍ ያዳመጠ፥ ለምን በእምነትም ይሁን በጐሳ ቀለም እውነትን ማጠልሸት አይቻልም እንዳልኩ ይረዳል።
መቼም ዘንድሮ ሀገር ተፅዕኖ ፈጣሪና ተፅዕኖ ፈላጭ (ቀፋይ) ተደበላልቆበታል። ይህን ለሌላ ጽሑፍ ትቼ፥ ወደ “ፓለቲካው ተንታኝ” ጥናታዊ ቃለምልልስ ልመለስ። ግን “ምን ኣስር ጊዜ “ጥናታዊ” “ጥናቲዊ” ይላል?” እንዳትሉኝ፤ የእሳቸው እንጂ የእኔ ቃል አይደለም። ደግሞም ካላችሁም በሉ፤ እኔ ግን ለእርሳቸው ያሉኝን ብዥታዎች ላቅርብ፦
እንደርሶ “ጥናታዊ” ቃለምልልስ፦ “ብሔርተኝነት” አቶ ጌታቸው ረዳ ሲጋልቡት አደጋ ያለው የነብር ጫንቃ፥ አቶ ጃዋር ሲጋልቡት ግን ያለኮረቻ የሚደላ የድንጉላ ፈረስ ጀርባ ሊሆን የቻለው በምን ስሌት ነው?
ትላንት፦ “ሰይ ባንከረባብት … ለሰፋሪው አንገት!“ ብሎ ሜንጫ እንደ VC ጠጠር ሲወረውርና ሲያስወረውር የነበረ፥ ዛሬ “በእግዜር?!” ብሎ ለምኖ ባይሰማ መውዜር ያነሳን የመብት ተሟጋች ለመተቸት ምን የሞራል ብቃት አለው? አቶ ጃዋር … በሚኒልክ ሞት ይሁንብዎ እስቲ እውነቱን ይንገሩን፥ በግብረገብም ይሁን በግብግብ ከሁለቱ የቱ ይከፋል? ይኽው … ይሰማዎታል? “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ብሎ ይተርታል ያልተጠየቀው አንባቢ ተቅለብልቦ ሲመልስ። በእስክሪቢቶ የተፃፈው ህገመንግስት በክላሽ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚንስትሩ የነገሩንን እርሶም አስምረውበታል። “ግሩም ነው!” ይላሉ አቶ ገረመው … እስቲ የእርሶን ተግባርና ምግባር እያወቀ ይህን ዲስኩር ተሻምቶ የሚገዛው፦ የኣማራ? የትግራይ? የጉራጌ? የሱማሌ? የኣፋር? የወላይታ? የሲዳማ? የትኛው ወጣት? የትኛው ፋኖ? ኢጀቶ ወይንም ዘርማ እንደሆነ በሂደት የምናየው ይሆናል።
ይህቺ የመጨረሻ ጥያቄዬ ናት፦ ንብረቱን በሌባ የተቀማ፥ ዓመታትን ቆጥሮ ሀቁን አግኝቶ የንብረቱ ጌታ ቢሆን፥ ለፍትህና ለአምላኩ እንጂ ለፍርድ- ቤቱ ዳኛ ባለዕዳ የሚሆነው በየትኛው “ ፍታብሔር” ነው? ነፃነት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ሳይሆን የኣንድ አምላክ ነፃ ችሮታ ነው፤ የእያንዳንዱ ዜጋ ንብረት! የሰው ልጅ ይህንን በረከት ሲነፈግ በሀይልም ይሁን በሀይ-ባይ (ሸምጋይ) ለማስመለስ ቢጥር “ወንጀለኛ” ሆኖ አይቆጠርም። የህወሃት ወንበር መነካት ያልነበረበት የአርያም መንበር ነበር ብለን ካላበድን በስተቀር፥ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ (ነፍስ ይማር) ቀድሞ ለጠነሰሰው መፈንቅለ መንግስት ወንጀለኛ፤ ከእስር ሲፈታም ለማንም ባለዕዳ ሆኖ ሊቆጠር አይገባም። ጄነራሉ ለመብቱ መፈንቅለ-መንግስት አስቦ አይደለም ምድርን አጋይቶ በረመጡ ክዋክብት እንኳ ቢቀልጡ፥ “ከእስር ፈታሁት” ብሎ የሚፈትል ዳኛ መሳይ ቀማኛ እንደባለውለታ ሊቆጠር አይገባም። ያውም … ብቻ ይቅር፤ ለነገ ላሳድረው።