Post

ፊኛዎቹ …

ፊኛዎቹ …

By Admin

ፊኛዎቹ …

በህወሀት ሥርወ-መንግስት፦ ያለ ጥፋቱ  የታሰረ  ዜጋ  ፍትህ  ፈላጊ  እስረኛ  ሳይሆን  ትዕይንት  አድማቂ  ፊኛ  ሆኖ  መቆጠር ከጀመረ  ሰንብቷል። ያም  ቢሆን  ግን ለአቶ  አንዳርጋቸው  ፅጌና ቤተሰቦችቻቸው  በሙሉ  ዳግም  በአካል  ስለተገናኛችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ።   

ከሦስት ዓመታት በፊት፥  በወቅቱ  የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የነበሩትን Barack Hussein Obama’ን ለመቀበል፥ ህወሃት ከሰሌን ያልተሻለ  ዥጉርጉር ስጋጃ  ዘርግታ ሽር ጉድ ስትል፥ ለትዕይንቱ ማድመቂያ  በአጅብ  ሽብ  አድርጋ ያወጣችው  የተነፋ ፊኛ ሳይሆን  የግፍ  እስረኛ  ነበር። አስማማው ኃ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ስድስት ጦማርያን በኣንድ ክር ታስረው ወደ ሰማይም ባይሆን ወደ ቤተሰብ ተለቀዋል።

ከወራት በፊት፥ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሹመታቸው ማግስት ሰሜን ተጉዘው፥ ሰውና ንብረት አንድደው ሊያከስሉ ሲማማሉ “እጅ-ከቦምብ” የተያዙ እስረኞችን “ስለወንጀላቸው ሳይሆን ስለትግራይ ህዝብ ክብር ማድረግ የሚገባንን እናደርጋለን ” ሲሉ ብሰማ፥ እየሱስን ከጉባዔው መሐል  ፈልጌ ስላጣሁት እንጂ፦  ጠቅላይ ሚንስትሩ ንጉስ ጲላጦስ፣ ተፈቺዎቹም በርባንን  መስለው ሊታዩኝ  ሰመመን  ጀማምሮኝ  ነበር።    

ይኸው ትላንት ደግሞ፦ ወንዝ ተሻግረው፣ ሰማየ-ሰማያት ቀዝፈው፣ ብሔራዊ ብቻ  ሳይሆን  አለም-አቀፋዊ  ህግ  ጥሰው ያፈኑትን እስረኛ- ለትዕይንት  ማድመቂያ  እንደተዘጋጀ  ፊኛ በግንቦት ሃያ ዋዜማ ለቀውልናል። ምክንያት እየተፈለገ፣ ክብረ በዓል እየተጠበቀ እስረኛን በአጀብ መፍታት ልማታዊ ልማድ ሆኗል። አሁን  አሁንማ፥  ያልታረሙ  ባለስልጣናት  ከማረሚያ ቤት ጀርባ በገፍ የሚያጉሯቸው ንፁሀን ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ፥ በየአደባባዩ በሰልፍና ጩኸት እሮሮ ከማሰማት ይልቅ ህወሃት የምትፈራው  እንግዳ  አሊያም  የምትዘክረው  ጽዋ እንዲመጣ  መፀለዩ  ሳያዋጣ አይቀርም።    

ይህን ማለቴ ግን – እስከዛሬ  የተጓዝንበትን  ልማድ  ለማስታወስ  እንጂ፡ አዲሱ  ጠቅላይ  ሚንስትር  ዶ/ር  አብይ  አህመድ  “ማሰር  ቀላል  ነው፥ መፍታት  ግን  ይከብዳል ”  ያሉትን  እውነት ለመተቸት አይደለም። ያላጠፋን  እስረኛ  ፈቶ  መልቀቅ  የሚያስመሰግን እርምጃም  ባይሆን፥  ህወሃት  በመሸገችበት ከተማ ግን እስረኛን አርነት ማወጣት ቀርቶ በአካል ተገናኝቶ፣ ጠይቆ መውጣት የሚቀል ተግባር እንዳልሆነ በሚገባ እረዳለሁ። ስለዚህም  ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚኖረኝ መልዕክት፦  ባዶ-ስድስትም  ኦና፣  ባዶ፣  ሙዚየም  ሆኖ  እስከምናይ  ይህንን  ሰናይ  ምግባር ይግፉበት!  ነው።

የሚታየው  መሻሻል  ከመሪ  እንጂ  ከመርህ ለውጥ የመጣ  አይደለም …

እስቲ ሐሳበ-መንገዴንም  የዶ/ር አብይ አህመድን ሰሞነኛ ተግባር ተንተርሼ  ትንሽ  ልበል።  ጠቅላይ ሚንስትሩ በአዛዥነት የተረከቡት የቢሮውን  ወንበር ሳይሆን  የእስር  ቤቱን  በር እስኪመስለን ድረስ በሀገር ውስጥም  ሆነ  በውጭ  ሀገር  የታሰሩ  ዜጎቻችንን በጅምላ  በምህረት  እየፈቱና  እያስፈቱልን  ነው። ታዲያ ይኽን ማን ይጠላል? ኦሮምኛ  ቋንቋ እየለመድኩ ነውና፦ ገለቶሚ! ብያለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞም፡ ቀን  አልፎ  ቀን  ሲተካ፡  በቂ  ባይሆኑም  የአስቸኳይ  ጊዜ  አዋጁን  መነሳት ጨምሮ  ቀላል  የማይባሉ  ፖለቲካዊና ማህበራዊ  ለውጦችን እያየን  ነው። ይህ  የለውጥ ዳዴ  ቆሞ እንዲራመድ  ደግሞ  የሚደግፈውና   የሚደገፈው  እጅ  መነፈግ  አይኖርበትም ባይ ነኝ።

ጥቃት ወደ ማጥቃት በሚደረግ  ማንኛውም  ሽግግር  ውስጥ  ቅፅበታዊም  ሆነ የተራዘመ የመከላከል ተግባር በመሐል ይኖራል። በመከላከል ድልድይ ሳይራመዱ ከማጥቃት ወደ መጠቃት ወይንም ደግሞ ከመጠቃት ወደ ማጥቃት መሻገር አይቻልም። በእኔ እይታ፦ አሁን ያለንበት እውነታ የማጥቃት ወይንም የመጠቃት ሳይሆን፥ እንደ  ሀገርና ህዝብ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶቻችን ላይ የተከፈተብንን  ጦርነት  እንደመከላከል  ተግባር ሆኖ  እመለከተዋለሁ። የመከላከል ተግባር ደግሞ  ማሽነፍ  ሆኖ  አያዘመርም፥  መሸነፍም ሆኖ  አያስላዝንም። ይልቁንም  ይህንን ወሳኝ የመሸጋገሪያ ምዕራፍ በበለጠ ስልትና ብስለት ለድል ልንፋለምበት ይገባል። የተሰጠውን  እየበላ  ስለሚያለቅስ  “ብልጥ!” የተባለው ልጅም  ቢሆን አለቃቀሱን  ካላወቀበት ለትንታ የተጋለጠ፣ በሞትና ህይወት  ቀጭን ወሰን  ላይ የሚጫወት  “ሞኝ” መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።    

የምናየው  መሻሻል  ከመሪ  እንጂ  ከመርህ  ለውጥ የመጣ  አይደለም። ህወሃትማ የትላንቷ ህወሃት  ነች! ማንነቷም፣ ማኒፌስቶዋም  በቅርፅም ሆነ በይዘት ፍፁም አልተቀየረም። አዎንታዊ የሆኑ ለውጦች ሲታዩ፥ ዶ/ር አብይ አህመድን  መደገፍ  ህወሀትን  መንቀፍ  ነው።  ጉዳያችን  ከለውጥ  ኢንጂነሩና ከተግባሩ ነው። እሳቸው  ኣንድ እርምጃ  ጠጋ  ብለው “ተፎካካሪ” ሲሉን፥ ተፎካካሪዎቹ ደግሞ  ሁለት  እርምጃ  ወደኋላ  አፈግፍገን፥  የለውጡን  ወጋገን – የእሳት ወላፈን ነው እያልን  በጭፍን  ስንጠራጠር፥  ህዝብ “ተጠራጣሪ” ብቻ ሳይሆን “ቅናታዊ” የሚል ተቀጥላም እንዳይሰጠን ማስተዋሉ  ይበጃል። ፖለቲካ  ደግሞ  በቅን  ልቦና  እንጂ  በቅናት  በገና  ሲደረድሩዋት – ጆሮ የሚከረክር ጎርናና  ድምፅ  ነው  ያላት።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ብዙ ቢቀራቸውም መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ክህወሃት ፍላጐት ውጪ አመራሮች ለሚወስዱት በጎ እርምጃ ድጋፍ መስጠት ስንጀምር ደግሞ፥ ትልቁ  ህገ-መረናዊ አንቀፅ 39  ሳይሰርዝ በፊት – ክልላዊ ድንብር ቀድሞ እንደሚፈርስ ቅንጣትም አልጠራጠርም። ሲጀምር  የሁለት፣ ከዚያም የሦስት፣ እያለም የኣራትና ኣምስት … ክልሎችን  ውህደት የምናይበት  ጊዜ በደጅ ነው።

ሰባተኛዋ የሜቴክ ቦርድ አባል ሆኜ እንደምሾም …

ይህን ስል ግን፥ አዲሱ  ጠቅላይ  ሚንስትር  እየወሰዱት  ያሉት  እያንዳንዷ  እርምጃ  ከመርህና  ፍላጎታችን ጋር ፍፁም የተጣጣመች ናትና፥  ከድጋፍም  አልፈን  ዶክተሩ 132ኛው የ-Nobel Peace Prize  ተሽላሚ  እንዲሆኑ  ከወዲሁ  ጥቆማና  ቅስቀሳችንን  እንጀምር  ማለቴም አይደለም።  ጠቅላይ  ሚንስትሩ  ተሳስተዋል ብለን ስናምን  መቃወምም  አግባብ ነው። ለምሳሌ? ብትሉኝ፦ የወይዘሮ  አዜብ መስፍን (የማዘር ጠገራ) ሹመት  በእጅጉ አስከፍቶኝ አልፎአል። ለምን? ስል መርምሬና ተመራምሬ  ሁነኛ ምክንያት  ስላጣሁለት  ወደ  መላምትም አዝግሜ  ነበር።

በአንድ  አጋጣሚ ዶ/ር  አብይ አህመድ  “ሰባተኛው የኢትዮዽያ  ንጉስ  አንተ ነህ ተብዬ ነበር ” ባሉበት ንግግራቸው፥ ፕሮፌሰር ሳሞራ የኑስን ጠቅሰው “ንጉስ ስሆን እንዲህ ትሆናለህ እለው ነበር ” ያሉትን አስታወስኩና  … እኚህ  አልኮል  የማይቀምሱ  ንጉስ፥  በአደይ ሮማን ሚጥሚጣ ሞቅ ብሏቸው፡ ለማዘር ጠገራም፦ ንጉስ ስሆን  የ-MeTEC ቦርድ አባል ትሆኛለሽ  ብለው  ሳያስቡት ስተው፥ “የተናገሩት  ከሚጠፋ  የወለዱት  ይጥፋ”  በሚል  እምነታዊ ቃል ተጠርንፈው  ይሆን እንዴ  ብዬም  አስቤ  ነበር።  የከርሞ  ሰው ካለን፥  ወይዘሮዋም  ኣንድ  ቀን  በአደባባይ፦  ሰባተኛዋ የሜቴክ  ቦርድ  አባል ሆኜ  እንደምሾም  አውቅ  ነበር  ብለው  ሲመሰክሩ  እንሰማቸው  ይሆናል።     

ወልቃ የትም አትሔድ …

ከላይ ከተነሳሁበት ሐሳብ ብዙ ርቄያለሁና፥ የአቶ አንዳርጋቸው ከቤተሰብ ጋር መቀላቅል የሰጠንን ደስታ በጠጅም ባይሆን በአዝማሪ  ግጥም  አወራርደነው  ብንለያይስ? ምን ይለናል? በምናቤ  አንድ የሰሜን ሳዱላ ከጎኔ አስቀምጫለሁና – እናንተም በምናባችሁ ሁለት ወንድና ሴት አዝማርያን አብረውን እንዳሉ አስቡ።   ተቀበል! ልበል ሳዱላዋን ተሽቀዳድሜ …

ተቀበል!

በላይ፣  አባ-ወራ … ሆነን  በጎጆችን
እንዳላዘዝንበት … በእልፍኝ  በጓዳችን
ዘንድሮስ  ተሸነፍን
ዘንድሮስ  ተነጠቅን
ሴቲቱ-መራችን

ተቀበይ! 

ሴቲቱም  ብትለኝ … በድንግልናዬ
ለአይንህ  ባትታይም … ማጌጫ  አልቦዬ
ተጣብቃለችና … ከስጋ  ከአጥንቴ
ወልቃ-የት  አትሄድ … ሸርተት  ብላ ተግሬ

Comments are closed.