Post

ፌዝቡክ (Fazebook)

ፌዝቡክ (Fazebook)

By Admin

ሰሞኑን ድርብ ብቻ ሳይሆን ድርብርብ በዓል ነው። ለምን ዛሬ የፖለቲካውን አንቺሆዬ አርግበን በማህበራዊው የ”ትዝታ ኖታ ትንሽ ፈታ አንልም? አንድአንዱ ፖለቲካ’ኮ እንደ ካቲካላ ነው፤ ሲበዛ ያሰክራል። በተለይማ የእኛ የአፍሪካውያኖቹ የፖለቲካ ካቲካላ መንደር፣ ጓዳ ውስጥ ስለሚጠመቅ አልኮሉ ብዙ ነው። ስለዚህ እስቲ በፌስቡክ ዙሪያ ስለታዘብኳቸውና ሰለምታዘባቸው ዕውነታዎች ሁሉንም ባይሆን ጥቂቶቹን አንስቼ ለዕረፍት ያህል እናውጋ።

መቼም ይኼ መከረኛ ፌስቡክ (Facebook) ላይፍቡክ (Lifebook) የተባለ ይመስል ከውልደት እስከ ሞት፣ ከሠርግ እስከ ፍቺ የማይለጠፍበት የህይወት ክስተት የለም። ከጥቂት ቀናት በፊት ኣንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ feeling sick የሚል ማስታወሻ post አድርጋ ተመለከትኩና አይዞሽ – ይማርሽ ብዪ ፌስቡካዊ ግዴታዬን በኮመንት ለመወጣት ወደ ታች ወረድ ስል 189 Like አየሁ። ትንሽ ግር አለኝ። ይቺ ልጅ feeling sexy ይሆን እንዴ ያለችው ብዬ ሰባራ መነፅሬን ከፍ ዝቅ እያደረኩ ሁለት ሶስት ጊዜ ደጋገሜም አነበብኩት። አልተሳሳትኩም feeling sick ነው የሚለው። አሁን ሰው ህመም ይሰማኛል ሲል Like ማደረግይዞሽ ይሂድ!  ከማለት በስተቀር የተለየ ትርጉም አለው? ይህን ያህል ህዝባችን በሃያ-ኣምስቱ ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ከመራራት ወደ ማሟረት ተሽጋግሯል ማለት ነው? ሌላው ቢሆን’ኮ “አይዞሽ” ከማለትም አልፎ፡ በደንብ ጠይቆና አጣርቶ ወረርሽኝም ከሆነ ሳይወረር በቶሎ ይወረወራል። ሁኔታው ቢያስገረመኝም ያው ተያይዞ መፈሰስ ባህላችን ነውና ኮመንቱን ትቼ እኔም እንደ ጓደኞቼ “ፖስቱን” Like አድርጌ አለፍኩ።

እኔማ አንዳንዴ ከሀገር የተባረርኩት ዱሮ ከጣልያን ጋር አብሬ እንደሆነ እስኪመስለኝ ድረስ ነገር-ዓለሙ ሁሉ ተቀያይሯል። ፌስቡክ ላይ የማየው ወጣት ሁሉ በትምህርት ደረጃው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ነው፤ ቢያንስ ባለ ኣንድ ዲግሪ። ዱሮ በእኛ ጊዜ ኮሌጅ ወይንም ዩኒቨርሲቲ የሚገባው በነጥብ ነበር። አሁን በዕድሜ ሆነ እንዴ?

የፌስቡክ ነገር ሲነሳ የሁሉም ኢትዮዽያዊ ፎቶ ስብስብ (album) ውስጥ የማይጠፋ ኣንድ ምስል አለ። የሃገራችን ባህላዊ ምግብ። እንጀራ በሉት ጥሬ-ስጋ፣ ክትፎ፣ ቅንጬ ወይንም ገንፎ ብቻ አንድ የምግብ ዓይነት አይታጣም። መለጠፍ ማስተዋውቁ ባልከፋ ግን ለምን ምግቡ ብቻ? ኢትዮዽያውያኖችን ከሌላው የአዳም ዘር ልምድና ባህል ለየት የሚያደርገን አመጋገባችን ብቻ ነው እንዴ? ባህላዊ ልብሱስ? ጌጣጌጡ? ጐጆ – ገዳማቱ? አዕዋፍት – አራዊቱ? አሃዝ – ፊደላቱ? ሳይንዛዛ በዚሁ ላብቃ።

በአዘቦቱም ቀን ሆነ እንዲህ ባለ የበዓል ሰሞን ፌስቡክ ላይ የሚለጠፈውን ፎቶና ቪዲዮ ስመለከት አንድ የሚያስገርመኝ ነገር አለ። ለምንድነው ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ፎቶ ስንነሳ ምግቡ ተበልቶ፣ መጠጡ ተጠጥቶ፣ ሳህን ብርጨቆው ከተራቆተ ቦሃላ የሚሆነው? ለምን ምግቡ ከመቅረቡ በፊት፣ ሲቀርብ ወይንም ደግሞ ቀርቦ መሀል ላይ ፎቶውን አንነሳም? ይህን የኣምስት-መቶ ብር ጥያቄ በተመለከተ የእኔ መላምት ሁለት ነው። አንድም በልተን ስንጠግብ ነው ማሰብ የምንጀምረው እና ድንገት ለስብስባችን ማስታወሻ ፎቶ እንደሚያስፈለገን የምንባንነው። ይህ ካልሆነም ጠግበን ወዝ-ደማችን ትንሽ መለስ እንዲል መዘየዳችን ሳይሆን አይቀርም። ለነገሩ አልኩ አንጂ ሀበሻ’ኮ በላም አልበላም ወዝ እና ውዝዋዜ የግሉ ነው።

ይህ ብቻም አይደለም። መቼም ሁሌ መስታወቶቻችን ነጮቹ ሆነዋልና እነሱን በምሳሌነት ባቀርብ እንኳ – ለበዓላቸው አሊያም ለስብስባቸው መታሰቢያነት የሚነሱት የካሜራ ፎቶ ፎከሱ (አትኩሮቱ) ፊታቸው እንጂ ምግባቸው አይደለም። ያም ሆኖ ግን ጠረፔዛው ላይ የቀረበው መስተንገዶ የድርሻውን ሥፍራ ይዞ በፎቶው ገፅ ላይ በአግባቡ ይታያል። የእኛ ፎቶ pattern  ግን የተገላቢጦሽ ነው። ለመታሰቢያነት የተፈለገው የተበላው ምግብ እንጂ የበላነው ሰዎች እንዳልሆንን እስኪመስል ድረስ ፊታችን በጨረፍታ ነው የሚታየው። የፎቶውን ሦስት-አራተኛ ገፅ የሚይዘው፦ ሳህን ትሪና ብርጨቆ በወጣ-ወጥ ቀልሞ፣ ቅባት እንደ ጓንት እስከ ሰዓት ማሰሪያው የሸፈነው እጅ ይሆናል። ያኔ ታዲያ ምግብ-ቤቱ ስርዓት ያጣ ላቦራቶሪ፣ ተመጋቢዎቹም ከድንገተኛ ማዋለጃ ክፍል የወጣን የገጠር ጤና ጣቢያ ተቀጣሪ ነው የምንመስለው።

አንዳንዱ ምግብ መብላት ነፍስ እንደ ማጥፋት “ወንጀል ነው!” የተባለ ይመስል የቀረበለትን በሙሉ ዶግ-አመድ አድርጎት፣ የምግቡንም የጣቶቹንም አሻራ ከሳህኑ ላይ አጥፍቶ ሲነሳ የታደለ አስተናጋጅ ሳህኑን ወደ ማጠቢያው ሳይሆን ወደ መደርደሪያው ይዞት የሚመለስ ነው የሚያስመስለው። ሌላው በተቃራኒው የበላበት “ትሪ” ላይ አስምሮት የሚነሳው መነሻና መድረሻው ፍጹም የማያሰታውቀው ጥልፍልፍ የጣቶች ፈለግ – የምግብ ሳህኑን ከአየር ላይ የተነሳ የሻንጋይ (Shanghai) ከተማ የቀለበት መንገድ ያስመስለዋል። ጥቂቱ እንደ እኔ የተሳካለት ደግሞ የቀለምም ባይሆን የወጥ አርቲስት ሆኖ – ሽራ ላይ ሳይሆን ሸክላ ላይ Pablo Picasso‘ን የሚያንኳስስ ምን የመሰለ ሽጋ abstract ስሎ ብድግ ይላል።

ዱሮ ዱሮ አያቶቻችን ወጉን ሲያስተምሩንገበታ ንጉስ ነው ይሉን ነበር። አሁን አሁን ውጉዝ ነው የተባለ ይመስል የሰው ጣት እንደ ማርያም ጠላት ነው የሚያርፍበት። እንደው ለነገሩ “ምግብ ነበር” ብሎ ለማመሳከር የተረፈ የሚመስል ጎመን- ሰሜን፣ ክፉኛ ተነክሶ በተዓምር ያመለጠ ድንች- ደቡብ ተበታትኖ ለተመለከተ፡ እህል የተበላበት ገበታ ሳይሆን የጨበጣ ወጊያ የተካሄደበት የጦር አውድማአሳዳጊው እንጀራ የተቆረሰበት ሳይሆን አሳዶ ገዳዩ አግ’አዚ የዋለበት የሰላማዊ ሰልፍ ሜዳ ይመስላል። አንዳንዴማ ለወሬ ነጋሪ፣ ለለምኖ አዳሪ እንኳ አንዳይተረፍ ሆኖ የተቀጠቀጠውን ምግብ ስመለከት፡ እንዲህ ኣፍ በሌለው ሰላማዊ በሆነ አካል ላይ የምንወስደው ያልተመጣጠነ የሀይል እርምጃ (excessive force) ሰዎቹን ብቻ ሳይሆን እኛንም የሚያስከስስ፣ የሚያስጠይቀን ይመስለኛል። በምድሩም ባይሆን በሰማዩ ችሎት። ብቻ በአጠቃላይ አንዳንዶቻችን በምግብ ላይ ያለን ጠንካራ አቋም በመንግስትም ላይ ቢኖረን ኑሮ ወያኔ ሃያ-ኣምስት ዓመት አይደለም ሃያ-ኣምስት ሰከንድ አይሰነብትም ነበር።

ከፎቶው ወደ ቪዲዮው ስንሄድም እንዲሁ የራሱ ታሪክ አለው። ፊትን ላለማሳይት ይሁን ለማስጎምጀት ምክንያቱ በውል ባይገባኝም፥ የምግብ ሳህኑ ላይ ብቻ focus አድርጐ በቅርብ ርቀት የተቀረፀ (close-up) ቪዲዮ ስመለከት ግርምትም ፍርሃትም ይፈራረቁብኛል። አንዳንዱ እንጀራ ልክ እንደ Michael “Mike” Wazowski  የካርቱን ምስል ኣንድ አይን ብቻ ነው ያለውMike-Wazowski-32። ምን አለፋችሁ – ከወፍረቱ ጋር መሃል ላይ አንድ ቀዳዳ ብቻ ሰታዩ ገንፎ የቀረበ ነው የሚመስላችሁ። ታዲያ በዛ ላይ እንደ ሞፈር የወፈረ ጣት መሃል ለመሃል ሰንጥቆት ሲያለፍ ገራዶ የሚታረስ እንጂ ገራገሩ እንጀራ የሚቆረስ አይመስልም።

ስለ ምግብ፣ ግብዣ፣ ጉርሻና ፍቅር በተነሳ ቁጥር ሁሌም ትዝታዬ ስለሆነችው ኣንድ ሰው ላውጋችሁና ጽሁፌን ላጠቃልል። ልክ እንደ ጥፍርዋ ጥርሷም ጣትዋ ላይ የበቀለ የሚመስለኝ የሴት ጓደኛ ነበረችኝ። ፊታችን የቀረበውን እንጀራ ምነው አጥንት ሆነው በቆረጣጠምኳቸው በሚያስብሉኝ ለግላጋ ጣቶቿ ለደቂቃዎች ስታፈተለትለው ስመለከት፡ በጣቷ ቆርሳ የምትጎርስ ሳይሆን በጣቷ አላምጣ የምትውጥ ነበር የምትመስለኝ። ያንን ሁሉ ደቂቃ ታግሼ ጠብቄ ልታጐርሰኝ የምታነሳውን እህል ስመለከት ደግሞ ከማነሱ የተነሳ ለአፌ ሳይሆን ለአፍንጫዬ ቀዳዳ ያዘጋጀችው እስኪመስለኝ ድረስ ሴትነቷና የሴትነት ወጉ ያስገርመኝ ነበር። ታዲያ በእሷ አይን ዛሬ እነ “ዘበናይን” ስመለከት – አቤት አቆራረስ! አጠቃለሉን ሲያውቁበት! ለሰው ሳይሆን ለራሳቸው ነው የሚጐርሱት እንጂ። ውፍረቱ የሌባ ጐማ እንጂ የሴት ልጅ አካል በማይመስለው ጣታቸው ላይ ረጃጅም የአሞራ ጥፍር ሰክተው መዳፋቸውን የትራክተር መቆፈሪያ፣ የ excavator ኣፍ አስመስለውታል። ታዲያ በዛ እጅ air-tight ሆኖ እንደ ብረት አሎሎ እስኪከብድ ድረስ ተጠቅልሎ የሚጐረሰው እንጀራ ከጉሮሮአቸው ተንሸራቶ ሰፊ ጨጓራቸው ላይ ሲያርፍ እንደ መድፍ ይጮሃል።

ትንሽ ቆየት ስላለ ማንነቱን አሁን ለማስታወስ ብቸገርም አንድ ታዋቂ ጸሃፊ ሴት ልጅ ፊት ለፊቴ ተቀምጣ የጎድን አጥንት ስትግጥ ሳይ አልወድም፤ ታሰፈራኛለች ያለው ትዝ አለኝ። ምነው የአሁኗን ባየልኝ። የጎድን አጥንት ስትግጥ አይደለም የቅልጥም አጥንት ሳታላምጥ ስትውጥ አይቶ ሰርከስ እንደተመለከተ ቆሞ ያጨበጭብ ነበር። በሉ በሉ በዚህ ኣዲስ አመት ጋባዥ ወይም ተጋባዥ ዘመድ ከማጣቴ በፊት በዚሁ እንሰነባበት።

Comments are closed.