Post

ፍቅር ያሸንፋል ?!

ፍቅር ያሸንፋል ?!

By Admin

አንዳንዴ ሐሰት የሆኑ ሓሳቦችን አገላለፃቸው ስለተመቸን ብቻ ለዘመናት ተሸክመን ስናራምዳቸው እንኖራለን። ይህ የሚሆነው ደግሞ “ለምን?” እና “እንዴት?” ብለን ለመጠየቅ ስለማንፈቅድ ነው። ለምሳሌም፦  “an eye for an eye” የሚለውን ብሒል የመሸበት አስተሳስብ አድርገን በመመልከት፥ “ዓይን ያጠፋን ሰው አይኑን ማጥፋት … ዓይነ-ስውራንን ማብዛት ነው” ብለን as a rule of thumb ተስማምተናል። ትንሽ ቆም ብለን፣ ዓይናችንን ሳይሆን ዓይነ-ህሊናችንን ከፍተን ይህን ሓሳብ ብንመረምረው ግን … “ዓይን ያጠፋን ሰው ዓይኑን ማጥፋትየሚለው ኦሪታዊ ህግ ምድርን የሚሞላት በኣይናማዎች እንጂ በዓይነ-ስውራኖች አይሆንም። ይህ አመለካከት  ዛሬ የበራልኝ ዕውነት ሳይሆን ከዘመናት በፊት የተቀበልኩት እምነቴ ነው። ለማስታውስም ያህል፦ እንደ ኣውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ከፃፍኩት ፅሑፍ ኣንዱ ምዕራፍ እንዲህ ይነበባል:

An Eye for An Eye
As of me, an eye for an eye could not be a menace for the world’s blindness. Rather, it would be a security assurance for the world peace by forcing everyone to hold his/her eyes wide open to see and keep distance from injustice. For fear of loosing their sight, individuals mind what and how to trade each other. Particularly, in the world of politics, if we dream a just society, let the principle of fairness and equity rule our judgment. Pay back what you receive as you shall receive what you give. Do not excuse to return a penny less or complain to earn a penny more. That keeps the scales of justice in equilibrium. (Post link: AN EYE FOR AN EYE! July 14, 2015)

ዓለማችን … “ዓይን ያጠፋን ሰው ዓይኑን ማጥፋት” የሚለውን ሕግ እንደ ሦስቱ የትራፊክ-መብራት ቀለማት (አረንጓዴ – ቢጫና – ቀይ) ያለ ድንበር በሁሉም ሀገር ኣንድ ሆኖ እንዲተገበር ቢፈቅድ … ስለራሱ ዓይን ሲል እንደ ቆቅ ንቁ ሆኖ ዓይኑን ሳይከድን ለሌላው ሰው ዓይን የሚጠነቀቅ ግለሰብ ይባዛል  እንጂ፥ ብርሃኑን ለማጣት የሌላውን ዓይን ለማውጣት የሚንደረደር አይኖርም። ይልቁንም፦ ለሌላው ሰው ዓይን መጠንቀቅ የራስን ብርሃን እንደ መጠበቅ ሆኖ ስለሚተረጎም … ኣንድ ግለሰብ በብቸኝነት ስለራሱ ዓይን ከማሰብና ከመጨነቅ ይልቅ ሌሎች በሚሊዮንና አልፎም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ስለ እርሱ አይን ደህንነት ሲሉ አይናቸውን ሳይጨፍኑ ዘብ የሚቆሙ ‘ወዳጆች’ ይኖሩታል። በሌላ አገላለፅ፦ ስለራሱ ዓይን ደህንነት ሲል የሌላውን ዓይን ለማጠብ ካልሆነ በስተቀር ለማጥፋት የሚቸኩል የክፋት እጅ አይበዛም። 

ከላይ እንደጠቀስኩት፦ የሰዎች ተፈጥሯዊ ባህሪ ከጣዕም ይልቅ ሽታን ወይንም ደግሞ እይታን የሚያስቀድም ስለሆነ … ሽፋኑ ላማረ አስተሳሰብም ሆነ ቁስ የምንከፍለው ዋጋ “ለምን?” እና “እንዴት?” በሚል ሰፋ ያለ የገበያ ሚዛን ላይ ተሰፍሮ አይደለም። አንዳንዴ … የመርሆቻችን ስህተት ከራሱ ከሓሳቡ ግድፈት የሚነሳ ብቻ ሳይሆን ከአተረጓጎምና አረዳዳችንም ጭምር ነው። አንድ ሌላ ሓሳብ ላንሳ …     

ብዙዎቻችን … ዕድሜ፣ ፆታና ሓይማኖት ሳይለየን “ፍቅር ያሸንፋል!” ስንል እንዘምራለን። ይህ ደግሞ የሓበሻው  አዝማች ብቻ ሳይሆን ነጩም ቢሆን በራሱ ቋንቋ “love conquers!” ሲል የፍቅርን አፄነት ይመሰክርለታል። በእርግጥ እኔም ብሆን የፍቅርን ጉልበተኛነት አልክድም። ነገር ግን ከተሳሳተ መረዳት ለመዳን … “ፍቅር ያሸንፋል!” ሲባል ‘ከማን ጋር ታግሎ?’ ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ፍቅር የሚያሸንፈው ከኣፍቃሪ ጋር  እንጂ ከኣክራሪ ጋር ሲታገል አይደለም። ግራ ጉንጭህን ሲነድለው ቀኝህን ስጠው የሚለው ፍቅራዊ አስተምህሮት መጨረሻ … የሚቀጠቅጥህን አካል እጅ ያዝለው ይሆናል እንጂ ልቡን አያለዝበውም።  ስለዚህም፦ ተበዳይ በደሉ እንዲያባራ በበዳዩ ጭካኔ ልክ እራሱን ካላሰማራ በስተቀር ሺህ ጊዜ “ፍቅር ያሸንፋል” ሲል ቢጮህ ሰው አይደለም አምላክም ጆሮ አይሰጠውም። ለምን? ብለህ ብትጠይቀኝ … የእራሱ የአምላክ የሦስት ኣስርት ዓመታት “የፍቅር ያሸንፋል” ህይወት የተደመደመው “ኤሎሄ!” በሚል የሲቃ ጩኽት እንጂ “እፎይ!” በሚያስብል  የርሕራሔ በረከት አልነበረም። መነሳቱ ግድ ስለነበር ከሞት ተነሳ እንጂ አሳዳጆቹ ፍቅርን በጭካኔ ገድለውታል፤ ያውም ሰቅለው … ልክ እንደ ሻሸመኔው። 

የአክራሪን ግድያ፣ አፈና፣ መፈናቀልና ወከባ ለማሸነፍ  “ፍቅር” ጉልበትም ብልሃትም የለውም። ንግስናዬ መለኮታዊ፣ አገዛዜም ፍፁም ሰማያዊ ነው ብሎ በትዕቢት ለተወጠረ ግለሰብ … የህዝብ ሲቃ ልክ እንደ ማለዳ ወፍ ጩኽት ልብን የሚያሞቅ ሙዚቃ እንጂ ልብን የሚሰብር የፍቅር ልመና አይሆንም። በየመድረኩ “ፍቅር ያሸንፋል!” ሲሉ ብታዳምጣቸው … አማኝና ታማኝለፍቅር ያደሩ ሎሌ መስለው ከታዩህ … የኣንተም የፍፃሜ ቃል ከ”ኤሎሄ!” እና ከ“ወይኔ!” የተለየ እንደማይሆን በእርግጠኝነት እነግርሃለሁ። ምክንያቱም መጽሐፉ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም”  ይላልና።

ከኣፋቸው የሚወጣው – በጆሮህ የምትሰማው “አሜን!” እና “ሀሌሉያ!” የእምነት መለኪያ ሆኖ … ፍቅር የሚገዛቸው (የሚያሸንፋቸው) መስለው ከታዩህ ፍፁም ስተሃል። የፕሮቴስታንትን … በተለምዷዊም አጠራሩ የፔንጤን የእምነት መልክ ለመመልከት ሳይሆን ኃይሉን ለመረዳት ከፈቀድክ … ዛሬ እያሳደዱ “ፍቅር ያሸንፋል” ብለው የሚያወሩትን ሳይሆን፥ ትላንትና ተሰደው “ይህም ያንስበታል!” ሲሉ የሰበኩትን አማኞች አዳምጥ – ተመልከት። እነዚህ “ሁሉም የእኛ! እኛ ብቻ ኣንደኛ!” የሚሉት … በሙሴ በትር ቀይባህርን ተሻገረው የተስፋይቱን ምድር የወረሱ አማኞች ሳይሆኑ … በቄሮ ዱላ ትህነግን አባረው ኣራት-ኪሎ የገቡ ብሔርተኞች ናቸው። ፅኑ ፍልሚያ እንጂ ንፁህ ፍቅር የማያሸንፋቸው አራጆች!

*Feature image credited for Mark Battles (Dax Diss)

Comments are closed.